“የሕክምና ግብዓቶችን ማሟላት እና ባለሙያው ሙያዊ ሥነ ምግባሩን ጠብቆ አገልግሎት እንዲሰጥ እየሠራ ነው” ጤና ቢሮ

46

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ‹‹ቅን አገልጋይነት እውነተኛ የሕዝብ ፍቅር መግለጫ ነው›› በሚል መሪ መልዕክት የአገልጋይነትን ቀን እያከበረ ነው፡፡ የአገልጋይነት ቀን አስመልክቶም የቢሮው ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የተከሰቱ የሰላም መደፍረሶች፣ መፈናቀል እና ኮሮና ወረርሽ ማኅበረሰቡ ማግኘት የሚገባውን የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ፈታኝ ኾኖ ቆይቷል፡፡ በዚህም ማኅበረሰቡ አላስፈላጊ ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል ብለዋል፡፡

ኀላፊው እንዳሉት ቢሮው ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመሥጠት ጤና ተቋማትን በሰው ኃይል የሟሟላት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ መሠረተ ልማት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የሕክምና ግብዓቶችን ማሟላት እና ባለሙያው ሙያዊ ሥነ ምግባሩን ጠብቆ አገልግሎት እንዲሰጥ የአቅም ግንባታ ሥራ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የአገልግሎት ቀን ሲታሰብ ተገልጋዩ ማኅበረሰብ መብትና ግዴታውን ተገንዝቦ አገልግሎቱን እንዲያገኝ፣ አገልግሎት ሰጭ አካላትም ቀልጣፋ፣ ፈጣንና ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እያጋጠሙ የሚገኙ ችግሮችን በመለየት መፍትሔዎችን ለማስቀመጥ፣ ብልሹ አሠራሮችን፣ መድሎ እና እንግልት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ደግሞ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ የባለሙያውን የአገልጋይነት ስሜት ለማጎልበት እና አንድነትን ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ እንደኾነም ነው ኃፊው ያብራሩት፡፡

በአዲሱ ዓመት ቢሮው ተቋማዊና ሕሊናዊ ኀላፊነትን ለመወጣት እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችም በአዲሱ ዓመት ሙያዊ ሥነ ምግባርን አክብረው ማኅበረሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፈጣን ምላሽ፣ ፍትሐዊ ተደራሽነት እና በቴክኖሎጅ የታገዘ አገልግሎት ተቋማዊ አሰራር ይኾናል” ከተሞች እና መሰረተ ልማት ቢሮ
Next articleየቤት መሥሪያ ቦታ ለተሰጣቸው ማኅበራት የሊዝ ውል እና አጠቃላይ ካርታ ለመሥጠት እየሠራ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።