“ፈጣን ምላሽ፣ ፍትሐዊ ተደራሽነት እና በቴክኖሎጅ የታገዘ አገልግሎት ተቋማዊ አሰራር ይኾናል” ከተሞች እና መሰረተ ልማት ቢሮ

41

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተሞች እና መሰረተ ልማት ቢሮ በክልሉ ውስጥ በመሰረተ ልማት፣ በመኖሪያ ቤት እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ በክልሉ የሚገኙ 680 ከተሞችን የሚያገለግል እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የከተሜነት መስፋፋት የሚመራ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ በክልል ደረጃ በ18 ዳይሬክቶሬት እና በሌሎች ደጋፊ የሥራ ሂደቶች ተመሥርቶ እስከ ወረዳ የሚደርስ አገልግሎት ይሠጣል ያሉን የአማራ ክልል ከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ አቶ አሰፋ ሲሳይ ናቸው፡፡ የተቋሙ ተቀዳሚ ዓላማ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ የኾኑ ከተሞችን መፍጠር ነው የሚሉት ምክትል ቢሮ ኅላፊው መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የመኖሪያ ቤት እና የኢንቨስትመንት ዘርፎች የትኩረት አቅጣጫዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡

የከተሞች እና መሰረተ ልማት ዘርፉ ብልሹ አሠራር፣ ሌብነት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች የሚፈትኑት ዘርፍ ነው የሚሉት አቶ አሰፋ ከምናገለግለው ሕዝብ ያገኘነው የዳሰሳ ጥናት እና መረጃ የሚያመላክተውም ይህንኑን ሥር የሰደደ የአገልግሎት ችግር ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም በዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮች መፍታት እና ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲኾኑ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ለዚህም “ፈጣን ምላሽ፣ ፍትሐዊ ተደራሽነት እና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ተቋማዊ አሰራር ይኾናል” ተብሏል፡፡

ምክትል ቢሮ ኅላፊው በርካታ ባለድርሻ አካላት ባሉበት፣ ሰፊ ቅሬታ በሚስተናገድበት እና ያልተመለሱ ፍላጎቶች በሚስተዋሉበት ተቋም ሕዝብን ማገልገል ፈታኝ ቢኾንም በአዲሱ ዓመት ችግሮቻችን ደረጃ በደረጃ እየለየን ለመፍታት እንሠራለን ብለዋል፡፡ አዳዲስ ችግሮችን እና ተጨማሪ ቅሬታዎችን ላለመፍጠር በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ኅላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሠሩም ምክትል ቢሮ ኅላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የተቋሙ ቀጣይ አሠራር በተቻለ መጠን ከሰው ንክኪ በማራቅ ቴክኖሎጂን በስፋት ለመጠቀም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሰርተዋል ተብሏል፡፡ በቀጣይም ከተቋሙ ባለድርሻ አካላት፣ ከተገልጋዩ ሕዝብ እና በየደረጃው ከሚገኘው የዘርፉ ፈጻሚ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ያነሱት ምክትል ቢሮ ኅላፊው “በአገልጋይነት ቀን ላይ ኾኘ ሕዝብን ማገልገል ክብር እንደኾነ በድጋሚ መግለጽ እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያደረገች ያለችውን ለውጥ አደነቁ።
Next article“የሕክምና ግብዓቶችን ማሟላት እና ባለሙያው ሙያዊ ሥነ ምግባሩን ጠብቆ አገልግሎት እንዲሰጥ እየሠራ ነው” ጤና ቢሮ