
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ ባለው የአየር ንብረት ጉባኤ ንግግር ያደረጉ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያደረገች ያለችውን ተጨባጭ ለውጦች አድንቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ አንድ ድምፅ ለመሆን ወደ አንድ አይነት ተግባር መምጣት ይኖርባታል ብለዋል፡፡
አያይዘውም ለዚህ ደግሞ መልካም ተሞክሮዎችን ከሌሎች አህጉራት ከመጠበቅ ይልቅ፤ ከኢትዮጵያ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መማር ይገባል ብለዋል።
በአረንጓዴ ኃይል ልማት ዘርፍ ተፈጥሯዊ ምላሾችን በመስጠት ኢትዮጵያ በተግባር ካሳየቻቸው የቢሊየኖች ችግኝ ተከላ እና መሰል በዕቅድ የተመሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተሰሩ ልምዶች ሊወሰዱ ይገባል ብለዋል ጉተሬዝ።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር አክንውሚ አዴሲና፤ “የአፍሪካ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ድጋፍ ከጠየቃችሁ ፤እንደ ኢትዮጵያ በሚታይ ስራ ጉዳይ ላይ ጠይቁ” ሲሉ አንስተዋል።
የባንኩ ፕሬዘዳንት በምሳሌነትም ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ያለን የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም እንዴት ምርታማ መሆን እንደሚቻል በስንዴ ምርት ላይ የሰራችው ስራ ጠቅሰዋል።
የ28ኛው የአለም አየር ንብረት ጉባኤ አዘጋጇ ሀገር የተባበሩት አረብ ኤሜሬት የCOP 28 ፕሬዚዳንት ዶክተር ሱልጣን አልጀብር፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ማሳካት የቻለቻቸው ስራዎች ተሞክሯቸው ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን እንደ አለም ሊወሰድ የሚገባው ነው ብለዋል።
ኢቢሲ እንደዘገበው፤ በምግብ ራስን መቻልን ለማረጋገጥ ስርዓታዊ ምላሽ የተሰጠበት እና ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት እንደሆነም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!