
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በቅንነት ለማኅበረሰቡ አገልግልት መስጠት እንዲችሉ ለማስቻል የአገልጋይነት ቀን በመንግሥት ሠራተኛው እየተከበረ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ የአገልጋይነት ቀንን በቀልጣፋ አሠራር ለተገልጋዮች ምቹ አገልግሎት በመስጠት ነው ቀኑን እያከበረ የሚገኘው፡፡
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንችአምላክ ገብረማርያም ከአገልግሎት ጋር ተያይዞ በተለይም የመንግሥት ተቋማት ተገልጋዮችን በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት፡፡
አገልጋይነት በክልሉ ሕዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን እና ጥያቄዎችን ሳይውል ሳያድር መመለስን ያካትታል ብለዋል ኮሚሽነሯ፡፡
እያንዳንዱ አገልጋይ ከራሱ ጥቅም ይልቅ ለሕዝቡ መሥራት ከቻለ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቅሬታዎች እንዳይነሱ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ቅን አገልጋይ ኾኖ መሥራት ቅን ትውልድን ለመፍጠር ያስችላል ያሉት ኮሚሽነሯ በክልሉ እዚህም እዚያም እየታዩ ያሉ ችግሮች በቅንነት መጓደል የተፈጠሩ እንደኾኑ አስታውቀዋል፡፡
አገልጋዮች ተገልጋዮችን ከእጅ መንሻ እና ከዝምድና ይልቅ በቅንነት አሠራርን በመከተል እንዲሠሩ ኮሚሽኑ እየሠራ እንደሚገኝም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የአገልጋይነት ቀን ጳጉሜ 1 በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡።
ዘጋቢ፡- ብርቱካን ታየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!