
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ጳጉሜን ለኢትዮጵያ” ሀገራዊ ንቅናቄ በሀገሪቱ እየተከወነ ነው። ጳጉሜን አንድ የአግልጋይነት ቀን “ኢትዮጵያን እናገልግል” በሚል መሪ ሃሳብ አገልግሎት እየተሰጠበት ነው።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ክብረት ማህሙድ የአገልግሎት ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልእክት በ2015 በጀት ዓመት የነበሩ ችግሮችን በመቋቋም የተሻለ ገቢ እንዲሰበሰብ ላደረጉ የተቋሙ ሠራተኞች ፣ ግብር ከፋዮችና አጋር አካላት ምሥጋና አቅርበዋል።
በ2015 በጀት ዓመት 42 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅደው 38 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻላቸውንም ኀላፊው አስታውሰዋል።
በአዲሱ ዓመት አዲስ አሠራር ፣ አስተሳሰብ ፣ አዲስ የሥራ ወኔ እና አሠራር ይዞ ይመጣል ያሉት ኃላፊው የአገልጋይነት ስሜታችንን የበለጠ በማጠናከር በቁርኝነት ሥራችን እንሠራለን ነው ያሉት። አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎችና መሪዎች በአማራ ክልል የተሻለ ውጤት እንዲመጣ በትጋት እንዲሠሩ አሳስበዋል። በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ ያለ አድሎ ሕዝብን በቅንነትና ቁርጠኝነት በማገልገል ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ነው ያሉት።
አግልጋይነት ገቢ ከመሰብበሰብ በላይ እንደኾነ እንገነዘባለንም ብለዋል። ተልእኮችን በቅን አገልጋይነት የሕዝብ አጋር መኾን እንሻለን ነው ያሉት። ያለ መታከት ለመሥራት ቃል እንገባለንም ብለዋል። አጋሮቻችን ውጤታማ እንዲኾኑ እናግዛለን ፤ ለምንወደው ሀገርና ሕዝብ እድገት የበኩላችንን አስተዋፅኦ እናደርጋለን ነው ያሉት።
የአማራ ክልል አሁን ካለበት ችግር ወጥቶ ለተሻለ ልማት እንደሚሠራም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።ግብር የዜግነት ክብር ነውም ብለዋል።
እንደገቢዎች ቢሮ የታክስ አሥተዳደር ሥርዓቱ እንደዚምን እንፈልጋለን ያሉት ኃላፊው የታክስ አሥተዳደር ሥርዓት መዘመን ለገቢ አሰበሰቡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውና ግብር ከፋዮችንም ከእንግልት እንደሚታደግ ገልጸዋል። የተጀመረው ዘመናዊ የታክስ አሥተዳደር አገልግሎት በአዲሱ ዓመት እስከታችኛው መዋቅር ድረስ እንዲወርድ እንሠራለንም ብለዋል።
ተገልጋዮቻችን በአዲሱ ዓመት ከእንግልት ነፃ የኾነ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የግብር ከፋዮችን ጥያቄ ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!