በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት የረጅ ድርጅቶች ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ርእስ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጠየቁ።

141

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና የካቢኔ አባላቶቻቸው የተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ድርጅቶች ተወካዮችን ተቀብለው የፓናል ውይይት እያደረጉ ነው። ርእሰ መሥተዳድሩ በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት በአማራ ክልል የወደሙ መሰረተ ልማቶችን እና የደረሱ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ለተመድ ተወካዮች አስረድተዋል። በሶስቱም ዙር ጦርነት 522 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት መውደሙን አንስተዋል። ከንብረት መውደም በተጨማሪም ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ ቀውሶች መድረሳቸውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካዮች አስረድተዋል።

“አሁን ከጦርነቱ ወጥተን የደረሱ ውድመቶችን መልሶ በመገንባት ላይ እንገኛለን” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የደረሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ በመኾኑ የረጅ ድርጅቶች ሚና የበለጠ መጠናከር አለበት ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት 1 ቢሊዮን ብር መድቦ ትምህርት ቤቶችን፣ ጤና ጣቢያዎችን እና የውኃ ተቋማትን እየገነባ ቢኾንም ከደረሰው ጉዳት አንጻር በቂ አለመኾኑንም ገልጸዋል። የደረሰውን ኢኮኖሚያዊ እና ሰብዓዊ ቀውስ መልሶ በመገንባቱ ረገድ የረጅ ድርጅቶች ሚና የሚጠበቀውን ያህል እንዳልነበርም ርእሰ መሥተዳድሩ ለተመድ ተወካዮች አንስተዋል።

አማራ ክልል ከደረሰበት ውድመት ወጥቶ ወደ መደበኛ ልማት እንዲገባ ለማስቻል ተመድ ኤጀንሲዎች አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። ክልሉ በትኩረት ለሚሠራው የኢኮኖሚ ልማትም ኤጀንሲዎች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መልእክት አስተላልፈዋል።

ወደ ክልሉ ገብተው በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ተመድ ተወካዮችም በክልሉ ውስጥ ለተከሰቱ ችግሮች ሰብዓዊ እርዳታዎችን እንደሚያቀርቡ እና ለዘላቂ ልማት አጋር ኾነው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

ከተወካዮች መካከል የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አልአክባሮቭ (ዶ.ር) ድርጅቱ በአማራ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እና የዘላቂ ልማት ሥራዎች ላይ በትኩረት እንሚሠራ ተናግረዋል። በክልሉ በግብርና ሥራ፣ በመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በጤና እና በሌሎችም የልማት ሥራዎች ላይ የአጋርነት ሥራዎችን እናከናውናለን ሲሉም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ማቀዱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next article“ለተገልጋዮች ከእንግልት ነፃ የኾነ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነን” የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ክብረት ማህሙድ