ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ማቀዱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

39

👉መስከረም 14/2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሪያ ቀን ይኾናል ተብሏል፡፡

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016 የትምህርት ዘመን ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ማቀዱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡ የተማሪዎችን ምዝገባ በሕዝባዊ ንቅናቄ ለማስጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ከሰኔ 2015 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤቶች ድረስ ወርዶ ሲተገበር ቆይቷልም ተብሏል፡፡

የ2016 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባን ከነሐሴ 23/2015 ዓ.ም እስከ ጳጉሜን 3/2015 ዓ.ም ድረስ በሕዝባዊ ንቅናቄ ለማካሄድ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በዕቅድ ደረጃ ደርሷል ያሉን የትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ናቸው፡፡ በትምህርት ዘመኑም ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ታቅዷል ብለውናል፡፡

ዕቅዱ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን፣ በተለያዩ ጊዜያት ያቋረጡ ተማሪዎችን፣ በ2015 የትምህርት ዘመን የደገሙ ተማሪዎችን እና ነባር ተማሪዎችን ታሳቢ ያደረገ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው በርካታ አካባቢዎች የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡ በምሥራቅ አማራ አካባቢዎች ላይ የተማሪዎች ምዝገባ ሥራው በተሻለ መልኩ እየተከናወነ ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ኅላፊው አንዳንድ ትምህርት ቤቶችም የዕቅዳቸውን ከ80 እስከ 90 በመቶ አፈጻጸም መዝግበዋል ነው ያሉት፡፡

በ2016 የትምህርት ዘመን መርሐ ግብር መሰረት ከመስከረም 2/2016 ዓ.ም እስከ መስከረም 11/2016 ዓ.ም ድረስ የትምህርት ሳምንት ኾኖ ይቆያል ያሉት አቶ ጌታቸው የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እና የዕቅድ ትውውቅ መርሐ ግብር በየትምህርት ቤቶቹ ይደረጋል፡፡

መስከረም 14/2016 ዓ.ም ደግሞ የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሪያ ቀን ይኾናል ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመንግሥት ሠራተኞች የአገልጋይነት መንፈስን በመላበስ መሥራት ያጠበቅባቸዋል” የሰሜን ሸዋ ዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ
Next articleበሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት የረጅ ድርጅቶች ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ርእስ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጠየቁ።