
ደብረ ብርሃን: ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር ፍቅር ስሜት መገለጫዎች ውስጥ አንዱ ኀላፊነትን መወጣት እንደኾነ የሰሜን ሸዋ ዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ገልጿል፡፡
መምሪያው በተለይ የመንግሥት ሠራተኛው የተሰጠውን ኀላፊነት በሚገባ መወጣት እንደሚጠበቅበት ነው ያሳሰበው፡፡
የመምሪያው ኀላፊ ሜሮን አበበ የመንግሥት ሠራተኞች የአገልጋይነት መንፈስን በመላበስ ማገልገል እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
ለአንድ ሀገር መሰረቱ የሰው ኀይል መኾኑን ያነሱት ኀላፊዋ ብቃት ያለው የሰው ኀይል በመገንባት የሕዝቡን የመልካም አሥተዳደርም ኾነ የመልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነች በምትገኝበት በዚህ ወቅት የመንግሥት ሠራተኛው 8 ሰዓት በሥራ ገበታ ላይ በመገኘት የተሻለ ሥራ መሥራት የሚጠበቅበት መኾኑንም ነው የገለጹት፡፡
መጭውን አዲስ ዓመት በዞኑ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የአገልጋይነት ስሜትን በመላበስ ፣የሥራ ፈጠራ አቅምን በመጠቀምና ከፍተኛ አገልግሎት ለተገልጋዮች በመስጠት ውጤታማ ሥራ እንዲሠሩ ኀላፊዋ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!