የፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ ለሚተጉ ምስጉን አገልጋዮች ምሥጋና እንደሚገባቸው የባሕር ዳር ተገልጋዮች ተናገሩ።

13

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የፍትሕ ተቋማት አገልግሎታቸውን ለማዘመን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ስለመኾናቸው የሚናገሩት የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱ ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ነው ያስረዱት፡፡

የፍትሕ ተቋማት ሕዝብን ያለልዩነት ማገልገል እንዳለባቸው አስበው በዚያ መጠን መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ያነሱት አገልግሎት ተጠቃሚዎቹ አሁንም ግን አገልግሎቱ ይበልጥ መዘመን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

አገልግሎት ፈልገው ወደ ፍትሕ ተቋማት መምጣታቸውን የነገሩን አቶ አሰፋ ውበት የሚፈልጉትን አገልግሎት አግኝተው መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡

ብዙ ጊዜ የፍትህ ተቋማት ላይ አገልግሎት ፈላጊው ስለሚበዛ ያንን ጫና ተቋቁመው የፍትሕ ባለሙያዎች ሁሉም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የሚያደርጉትን ጥረት አደንቃለው ብለዋል አቶ አስፋ፡፡

አገልግሎት ተጠቃሚው እንዳሉት ብዙ ጊዜ አንድን ጉዳይ የተለያዩ ዳኞች እንዲይዙት መደረጉ የተሻለ አሠራር ስለመኾኑም ነግረውናል፡፡

በተለይም ጉዳዩ ውስብስብ በሚኾንበት ጊዜ ዳኞች ተባብረው ጉዳዩን ማየታቸው የተሻለ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚያግዝም ነው ያላቸውን እምነት የተናገሩት፡፡

አቶ ሲሳይ ሙሉዓለም በበኩላቸው አገልግሎት ፈላጊው የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ የሚሠራው ሥራ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የፍትሕ ፈላጊዎች ፍትሕን ፍለጋ ሲመጡ ሳይንገላቱ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራርም መዘርጋት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል፡፡

የፍትሕ ባለሙያዎች ፍትሕን ለሚፈልጉ ሁሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ለሚያደርጉት ጥረት ማመስገን እንደሚገባ ገልጸው በዛሬው የአገልግሎት ቀን ልናመሠግናቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡

አገልግሎት ፈላጊዎቹ እንደሚሉት አገልግሎት የሚሰጥን አካል ለአገልግሎቱ እውቅና መስጠት አገልግሎቱ እንዲጠናከር እና የበለጠ እንዲሠራ እንደሚያደርገው ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡

በምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ተወካዮች ወደ አማራ ክልል ገቡ።
Next article“እናገለግልሽ ዘንድ ስለተፈጠርን እናመሰግናለን!”