
‹‹ዓፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የጀግንነት አባት ናቸው፡፡›› ወጣቶች
በክፍለ ዘመኑ ኃያላን ከነበሩት የዓለም መሪዎች መካከል ከግንባር ቀደሞቹ ይጠቀሳሉ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ብዙ ጥረዋል፡፡ ጠንካራ መሪ ላልነበራት ኢትዮጵያ ጠንካራ መሪ ሆነዋታል፡፡ እኚህ ጀግና ንጉሥ የተወለዱት በዛሬዋ ቀን ጥረ 6/1811 ነበር፡፡ ዓፄ ቴዎድሮስ ለሃገራቸው ሁሉን አድርገዋል፡፡ በተለይ ለዛሬው ትውልድ አርዓያነታቸው የትየለሌ ነው፡፡
ታዲያ ወጣቱ አርዓያነታቸውን በወጉ ተረድቶት ይሆን? ከሆነስ ምን ተማረ? ያነጋገርናቸው ወጣቶችም ‹‹ዓፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ አንድነትና ጀግንነት አባት›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡ ዓፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከነበረችበት የጭንቅ ዘመን ያወጡ የቁርጥ ቀን ልጅ እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በአሁኑ ዘመን እንደ ዓፄ ቴዎድሮስ አይነት መሪ እንደሚያስፈልጋት ወጣቶች ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዓፄ ቴዎድሮስ ለሀገር ክብርና አንድነት ሲሉ የህይወት ዋጋ ከፍለዋል›› ያሉት ወጣቶቹ የዘመኑ ትውልድም ለሃገሩ የሚገባውን መስዋዕትነት መክፈል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ›› አሉ ወጣቶቹ ‹‹በእርግጥ በዚህ ዘመንም መስዋእትነት የሚከፍሉ ወጣቶች በየቦታው ሞልተዋል፤ ነገር ግን ዋጋ ሚከፍሉለትን ጉዳይ መለየት፣ የከፈሉት መስዋእትነትም በትክክል ዋጋ እንዲያገኝ ማድረግ›› ብለዋል፡፡
በዚህ ዘመን ያሉት መሪዎች የቆሙለት አላማ ግልጽ እንዳልሆነና ሕዝቡም እነርሱን ተከትሎ ለማጀገን እንደሚቸገር ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወጣቱ በዘረኝነት መንፈስ የተከፋፈለበት ዘመን ነው›› ያሉት ወጣቶቹ፣ ወጣቱ ወደ አንድትና ወደ ሃገር ፍቅር እንዲመጣ በትኩረት መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ አንዲት ጠንካራ ሃገር ለመፍጠር የአባቶቹን ታሪክ፣ የኢትዮጵያን ማንነት ማወቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ወጣቱ ከዘረኝነት በፊት ‹‹ እኔ ማን ነኝ ? የቀደመው የኢትዮጵያውያን ማንነትስ ምን ነበር? ›› ብሎ መመርመር እንደሚገባም ነው ስገነዘቡት፡፡
በተለይም ባለፉት ዓመታት በወጣቱ ላይ የደረሰውን የስነ ልቦና ቀውስ ለማስተካከል የአባቶቹን ታሪክ በማስታወስ ሌላ አኩሪ ታሪክ መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪው ዓለማየሁ እርቅይሁን ‹‹ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ በህይወት ባይኖሩም ሥራዎቻቸው ዘመን ተሻጋሪና ህያው ናቸው›› ብለዋል፡፡ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የነበሩበት ዘመን አስቸጋሪ እንደነበር የተናገሩት ዓለማየሁ አንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ለመመስረት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው አስረድተዋል፡፡ ዘመነ መሳፍንት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሁለንተናዊ ውድቀት የታየበት ነበር ፤ ዓፄ ቴዎድሮስ በአስቸጋሪው ዘመን አስደናቂ ራዕይ ይዘው የመጡ ታላቅ ሰው ናቸው ተብሏል፡፡
እንደ አቶ አለማየሁ አስተያዬት የአሁኑ ትውልድም ከሚያለያየው ይልቅ በሚያስተሳስረው በርካታ ነገር ላይ በማተኮር መሥራት አለበት፡፡ ሕዝቡም ለዘመናት ያስተሳሰረውን የጋራ አንድነት በማሰብ ከዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ጠንካራ የስነ ልቦና ልዕልና መማር ይገባዋል፡፡ ታላቅ ሃገራዊ ራዕዩን በማዬት ለሃገር ክብር እና አንድነት መሥራት አለበት የሚለው የወጣቶች እና የታሪክ ተማሪው ዓለማሁ ሀሳብ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ከንዴ