
ባሕር ዳር: ጷጉሜን 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተሠማሩበት የሙያ መስክ የተሻለ አገልግሎት በመስጠት የማኅበረሰቡን ጤና መጠበቅ ኀላፊነትን ገና ከተማሩበት ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የምርቃት ካባቸውን ሲደርቡ የሚገቡት ቃል ኪዳን ነው፡፡ “ሕዝባችንን በታማኝነት በቅንነት ያለ አድሎ ለማገልገል ዝግጁ ነን” ብለው በሕዝብ ፊት በወላጆቻቸውና ባስተማሯቸው መምህራን ፊት መነሳንሳቸውን ከግራ ወደ ቀኝ አዙረው ቃል ገብተዋል። በተሠማሩበት ሙያ ታካሚዎችን ደከመኝ ሳይሉ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የዘንዘልማ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ኀላፊ ክንዳለም ያየህ ከእነዚህ መካከል አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ክንዳለም በተቀመጡበት የኀላፊነት ቦታ ሁሉንም ሠራተኞች እያስተባበሩ በመሥራታቸው ማኅበረሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እያገኘ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከ10 ሺህ 900 በላይ የኅብረተሰብ ፍሎችን የሚያገለግለው የዘንዘልማ ጤና ጣቢያ በሥሩ ሁለት ጤና ኬላዎችን እና 45 በላይ ሠራተኞችን አቅፎ ይዟል፡፡ የአዋቂዎች፣ የሕጻናት፣ የነፍሠጡር እናቶች፣ የወባ በሽታ ምርመራ አገልግሎት የሚሠጠው ጤና ጣቢያው በየቀኑ ከ150 በላይ ታካሚዎችን ተቀብሎ አገልግሎት ይሠጣል፡፡
የዘንዘልማ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ክልሉ ችግር በገጠመው ወቅትም ሥራ አለማቆሙን ኀላፊው አንስተዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት እንዲያገኝ እየሠራን ነው ያሉት አቶ ክንዳለም ከአቅም በላይ የኾነውን ደግሞ አዲስ ዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በሪፈር ይላካል ብለዋል፡፡ “የገባነውን ቃል በተግባር በመተርጎም ሳይማር ያስተማረንን፣ ሳይኖረው ያበላንን ማኅበረሰብ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረግን ነው” ብለዋል አቶ ክንዳለም፡፡
ሌላው አሚኮ የአገልግሎት አሰጣጡን የቃኘበት የሹም አቦ ጤና ጣቢያ ነው። የጤና ጣቢያው ኀላፊ ዓለም አሰፋ ጤና አጠባበቅ ጣቢያው በቀን እስከ 400 የሚደርሱ ታካሚዎችን አገልግሎት እንደሚሠጥ ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ዓለም ጤና ጣቢያው ተመላላሽ ታካሚዎችን ጨምሮ የቲቪ፣ ድሕረ ወሊድ እና የቅድመ ወሊድ፣ ቀላል ቀዶ ሕክምና አገልግሎት፣ የእናቶች እና ሕጻናት ምርመራ እና ድንገተኛ በሽታዎችን ያክማል ብለዋል፡፡ ሆስፒታሉ የአሥተዳደር ሠራተኞችን ጨምሮ 63 ሠራተኞች እንዳሉት የሚጠቅሱት ኀላፊዋ ወደ ጤና አጠባበቅ ጣቢያው የሚመጡ ተገልጋዮችን በቅንነት አገልግሎ እንደሚሰጡም አስረድተዋል፡፡
ክልሉ ችግር በገጠመው ወቅት ሥራ አላቆምንም የሚሉት ወይዘሮ ዓለም ኹሉም ሠራተኛ ለሙያው ክብር ሰጥቶ በችግር ውስጥ ኾኖም አገልግሎት መስጠቱን ተናግረዋል፡። ለዚህም ለሙያተኞች ከፍ ያለ ክብር አለን ነው ያሉት፡፡
ለሕሙማን የላቨራቶሪ እና የሲቪሲ ምርመራ አገልግሎት በሠፊው እንደሚሠጥ የገለጹት ኀላፊዋ ክልሉ አለመረጋጋት ውስጥ በገባበት ወቅት በርካታ ሰዎች ያለምግብ እና ያለውኃ እንደሠሩም ጠቁመዋል፡፡ የገባነውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ሙሉ አገልግሎት ሠጥተናል፤ በቀጣይም የገባነው ቃል ኪዳን ወቅት የማይሽረው በመኾኑ የበለጠ ለማገልገል ዝግጁ ነን ነው ያሉት፡፡ ጤና አጠባበቅ ጣቢያው በቂ የመድኃኒት አቅርቦት እና ሌሎች የምርመራ መሣሪያዎች በአግባቡ የተሟላለት በመኾኑ አገልግሎቱ እንደማይቋረጥ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!