
ባሕር ዳር: ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን እና 160 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው፡፡ ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡ በሥራው ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ተሳትፈውበታል፡፡
ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኮሚዲቲ ሰብሎች ተሸፍኗል፡፡
አርሶ አደር ደጉ እስተዚያ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ይጎዲ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ደጉ ሰብላቸውን በመንከባከብ ላይ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ ለበቆሎ የሚፈልጉትን ግብዓት ለማግኘት ተቸግረው ቆይተዋል፡፡ አሁን አካባቢው ወደነበረበት ሰላም በመመለሱ ማዳበሪያ እንደጨመሩ ነው ለአሚኮ ሃሳባቸውን ያካፈሉት፡፡ አካባቢው ለበቆሎ ምርት የተሻለ እንደኾነ የሚያነሱት አርሶ አደር ደጉ ባለፈው የመኸር ወቅት የተሻለ ግብዓት በመጠቀማቸው 24 ኩንታል በቆሎ ማምረታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ ዓመት በተፈጠረው የግብዓት መዘግየትም ኾነ የአካባቢው ሰላም አለመኾን በምርታቸው ላይ ችግር እንዳይኾን የሚችሉትን ኹሉ እያደረጉ መኾኑን ያነሳሉ፡፡ ሌሎች አርሶ አደሮችም በእሳቸው ልክ እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ አርሶ አደር ወንድሙ አሰሙ በላይ ጋይንት ወረዳ ዙርአምባ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ወንድሙ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ባቄላ፣ ምስር እንዲኹም ድንች ባለቻቸው ሁለት ሄክታር መሬት ላይ እያለሙ ነው፡፡
አንድ ኩንታል የአፈርና አንድ ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቅመዋል፡፡ ክልሉ በገጠመው አለመረጋጋት የሚፈልጉት ማዳበሪያ በወቅቱ ማግኘት አልቻሉም ነበር፡፡ አሁን የአካባቢው ሰላም ሲመለስ ያገኙትን አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ድንችን ሳይጨምር በሁሉም ሰብል ላይ ጨምረዋል፡፡ የስንዴ ዋግ ተከስቶ እንደነበረ የጠቆሙት አርሶ አደር ወንድሙ ምርታቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር በግብርና በኩል የቀረበላቸውን የስንዴ ዋግ በሽታ መድኃኒት መጠቀማቸውን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የድንች ምርትን ሳይጨምር 20 ኩንታል ምርት እንዳገኙ የሚያነሱት አርሶ አደሩ ዘንድሮም የተሻለ ምርት ለማግኘት በቂ እንክብካቤ እያደረጉ መኾኑን አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ ሰብሎች ምርት ለመሥጠት ምግብ የሚያሥፈልጋቸው ወሳኝ ቀናት መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በእነዚህ ቀናት ማዳበሪያ መጨመር ለምርታማነት አዎንታዊ ሚና አለው ባይ ናቸው፡፡
አንድ ማሣ በሠብል ከተሸፈነ ከ35 ቀናት ጀምሮ ማዳበሪያ መጨመር እንዳለበት የሚያነሱት ዳይሬክተሩ አቅም እና ጉልበት ያለው አርሶ አደር እስከ ሦሥት ጊዜ መጨመር እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ የተዘራው ማሳ አንድ አራተኛ ያህሉ እስከሚያብብ ድረስ ማዳበሪያ መጨመር ለምርት እድገት አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪ ዩሪያ የሚጨመርበት ማሣ እርጥበቱ ተመጣጣኝ መኾን እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ አርሶ አደሮች በእጃቸው የገባውን ማዳበሪያ አፈሩን እርጥበት እና የሰብሉን የእድገት ደረጃ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲጨምሩም አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አጀበ ስንሻው ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ አርሶ አደሮች እጅ መግባቱን ተናግረዋል፡፡
ለ2015/16 የመኸር እርሻ ጥቅም ላይ የሚውል 5 ሚሊዮን 296 ሺህ 670 ኩንታል ማዳበሪያ መገዛቱን ተናግረዋል፡፡
ለክልሉ ምርት ማሳደጊያ ከተገዛው ማዳበሪያ ውስጥ 2 ሚሊዮን 978 ሺህ 716 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 1 ሚሊዮን 965 ሺህ 449 ኩንታል የዩሪያ ማዳበሪያ በድምሩ 4 ሚሊዮን 934 ሺህ 165 ወደ አማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት መጓጓዙን ተናግረዋል፡፡ አቶ አጀበ እንዳሉት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከገባው ማዳበሪያ በድምር 4 ሚሊዮን 715 ሺህ 562 ኩንታል ማዳበሪያ አርሶ አደሩ እጅ ገብቶ ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!