
ጎንደር: ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ አሥተዳደሩ የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ በበኩሉ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት እንዲኖር እየሠራ መኾኑን አስታውቋል። በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የፋሲል ክፍለ ከተማ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን አሚኮ ቅኝት አድርጓል፡፡ አገልግሎት ለማግኘት በስፍራው ያገኘናቸው ተገልጋዬች በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ለእንግልት መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የፋሲል ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለባቸው ጀምበር በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ላይ በተገልጋዮች የሚነሱ ችግሮች መኖራቸውን አምነው ችግሩን ለመፍታት እየሠራን ነው ብለዋል። በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ሲሳይ እንዳሉት የቀደመው የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት እንከን የነበረበት እና ማኅበረሰቡን ለእንግልት የዳረገ ነበር፡፡
የ2015 በጀት ዓመት ችግሮችን በመለየት የሠራተኞችን ሙያዊ ብቃት ከፍ በማድረግ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ለመዘርጋት ሥራ መጀመሩን ነግረውናል። በዚህም በከተማ አሥተዳደሩ ከሚገኙ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት መካከል 17 የሚኾኑት የተሻለ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ ችለዋል ብለዋል።
የመምሪያው ኃላፊ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ለማኅበረሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ለመልካም አሥተዳደር ችግር ምክንያት እንዳይኾን ኃላፊነታቸውን በተገቢ መንገድ መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል።
ዘጋ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!