‹‹የታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ መንግሥት የተሰጠው የተምታታ መግለጫ ለጉዳዩ ትኩረት አለመሥጠቱን ማሳያ ነው፡፡›› የአማራ ሴቶች ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት እና የአማራ ሴቶች ማህበር

595
መንግሥት የዜጎችን በሀገሪቱ ላይ ተዘዋውረው የመሥራት ህገ መንግሥታዊ እና ሰብአዊ መብት የማሥጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ የአማራ ሴቶች ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት እና የአማራ ሴቶች ማህበር ጠይቀዋል፡፡
 
የአማራ ሴቶች ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት እና የአማራ ሴቶች ማህበር ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ በታገቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ አማራ ተማሪዎች ላይ ያለውን አቋም መንግስት ግልጽ ማድርግ እንዳለበትም ነው የጠየቁት፡፡
 
የአማራ ሴቶች ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ምትኩ እንደገለጹት መንግሥት የታገቱ ተማሪዎች መለቀቃቸውን ካረጋገጠ በክልሉ የሴቶች አደረጃጀቶች ድጋፍ እና እንክብካቤ እዲያደርጉ ጉዳዩ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ተማሪዎቹ ከአጋቾች ተለቅቀው ከሆነ ከወላጆቻቻው ጋር የማገናኘት ግዴታውን መንግስት እንዲወጣም ወሮ. እመቤት ጠይቀዋል፡፡
ታጋቾቹ ከተለቀቁ መንግስት ትክክለኛ መግለጫ በመስጠት ማኅበረሰቡን ማረጋጋት እንጂ ጉዳዩን አድበስብሶ ከመሄድ መቆጠብ እንዳለበትም ነው ኃላፊዋ የተናገሩት፡፡ ድርጊቱ ከማኅበረሰቡ እሴት ያፈነገጠ በመሆኑ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዜጎች በሀገሪቱ ላይ ተዘዋውረው የመስራት ሕገ መንግሥታዊ እና ሰብአዊ መብታቸውን በማስጠበቅ የመንግሥትነት ሚናውን መወጣት እንደሚገባውም ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
 
መንግስሥት በሀገሪቱ ላይ በሚፈጸሙ ችግሮች ላይ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ በመንግሥት ላይ ያለውን የማኅበረሰቡን እምነት ማሳደግ አለበት ያሉት ወሮ. እመቤት ማኅበሩ ልጆች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
 
የአማራ ሴቶች ማህበር ዋና ጸሃፊ ወይዘሮ አዲስ ጫኔ ደግሞ በመንግስት በኩል የተሰጠው የተምታታ መግለጫ ለጉዳዩ ትኩረት አለመሥጠቱን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ተማሪዎች በትክክል ተለቀውከሆነም በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ወላጆቻቸው ማወቅ መብታቸው በመሆኑ መነፈግ እንደሌለበት ጸሃፊዋ ተናግረዋል፡፡
 
ማህበሩ በአደረጃጀቱ በኩል የታገቱ ተማሪዎች ያሉበትን ጀረጃ ለማወቅ ጥረት እያደረገ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
በጸጥታ ችግር ምክንያት ከግቢው ለቅቀው እየወጡ የነበሩ በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ከእገታ እንደተለቀቁ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቢያሳውቅም አብመድ ባደረገው ማጣራት ተለቀቁ የተባሉ ተማሪዎችን ማግኘት አልቻለም፤ ወላጆቻቸውም ከልጆቻቸው ጋር እንዳልተገናኙ ነው የተናገሩት፡፡ ጉዳዩን ከስፍራው እየተከታተሉ ነው የተባሉ የጸጥታ አካላትም መረጃ ለመስጠት ፍላጎቱ እንደሌላቸው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ
Previous article‹‹ቴዎድሮስ ገና ገና ወደፊት በሚመጣው የኢትዮጵያ ትውልድ ልብ ውስጥ እንደ እንቁ ያበራሉ፤ ቴዎድሮስ የአንድ ትውልድ ብቻ ንጉሠ ነገሥት አይደሉም፡፡›› ደራሲ አቤ ጉበኛ
Next articleወጣቶች ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ አሻራዎች ምን ይማሩ?