“ጳጉሜን ለኢትዮጵያ” ንቅናቄ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች እንደሚከበር የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ገለጹ።

73

ባሕር ዳር: ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን “ጳጉሜን ለኢትዮጵያ” ንቅናቄ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ይከበራል ብለዋል። ጳጉሜን ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ ድልድይ ተደርጎ እንደሚወሰድ አንስተዋል።
በጳጉሜን ስድስቱ ቀናት ክልሉ ካለበት ችግር እንዲወጣ የምንሠራበት፣ ወደልማትና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎቻችን የምንገባበት፣ እርስ በእርስ የምንመካከርበት፣ በውይይት በሰከነ መንፈስ፣ በመከባበር ተመስርተን ከችግሮች ለመውጣት የምንሠራበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ያለፉትን ፈተናዎች እንደ ትምህርት በመውሰድ ቀጣይ ችግሮችን ፈትተን ፈተናዎችን ተሻግረን ወደ ተሟላ ቁመና የምንሸጋገርበት መኾን አለበትም ነው ያሉት።

የጳጉሜን ቀናት መነሻ በማድረግ ዓመቱን ሙሉ በትጋት እንሠራለን ነው ያሉት።

በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ሰላምን የማምጣት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። የልማት ሥራዎችም እየተከናዎኑ መኾናቸውን ነው የገለጹት።

አሁን ላይ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ተዘጋጅተዋል፣ ተማሪዎች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል። የጤና ተቋሙም መከላከልን መሠረት አድርጎ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በግብርና ምርት ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ምርት እንዲኖር እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።

በጳጉሜን አንድ የአገልጋይነት ቀን የሲቪል ሰርቪስ ዘርፉ አገልግሎቱን በተገቢው መንገድ የሚሰጥበት እና ከአሁን በፊት ሕዝብ ያማረሩ፣ ተገቢውን ግልጋሎት በመስጠት የሚፈቱበት እንደኾነም አመላክተዋል።

በሁለተኛው የጳጉሜን ቀን በመስዋዕትነት ቀን ለፀጥታ ተቋማት ልዩ ክብር የሚሰጥበት፣ ጀግንነት የሚዘከርበት እና ከፀጥታ ተቋማት ጋር የምንቆምበት ነውም ብለዋል። ለቀጣዩ ትውልድ ጀግንነት የሚወረስበት መኾኑንም አመላክተዋል።
በሦስተኛው የጳጉሜን ቀን በጎነት የሚታይበትና የሚዘከርበት መኾኑንም ተናግረዋል። የበጎ ሥራ እንዴት መከወን እንዳለበት የሚታይበት መኾኑንም ገልጸዋል።

ጳጉሜን አራት ደግሞ በአምራችነት ቀን የሕዝባችን ታታሪነት እና ሥራ ወዳድነት ይዘከራል ነው ያሉት። የአምራች ኢንዱስትሪው ሥራ የሚታይበት ቀን መኾኑንም ገልጸዋል። ከራስ አልፎ ለሌሎች እንዴት ተስፋ መኾን እንደሚቻል የሚዘከርበት ነውም ብለዋል።

ጳጉሜን አምስት በትውልድ ቀን ኢትዮጵያን አፅንቶ ያኖረው፣ አሁንም የተረከባት ትውልድ የሚዘከርበት ቀን ነው ብለዋል። አወንታዊ ነገሮችን በማጉላትና ለቀጣዩ ትውልድ በማስተማር በአሉታዊ ጉዳዮች ደግሞ ትምህርት በመውሰድ ቀኑ ይታወሳል ነው ያሉት።

በጳጉሜን ስድስት ቀን የአብሮነት ቀን እንደሚከበርም ተናግረዋል። የአብሮነት ታሪካችን የሚገለጥበት ቀን ነውም ብለዋል። ልዩነቶችን በማቻቻል አንድ የምንኾንበት፣ ፍቅርን የምንሰብክበት፣ መቻቻልን የምናመጣበት፣ በሰላም መኖርን የምንዘክርበት ነውም ብለዋል።

በጳጉሜን ቀናት ፍቅርን መስበክ ፤ አንድነትን ማጠናከር ይገባልም ነው ያሉት። ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በፍቅርና በአንድነት መኖር የሚያስችሉ ሁነቶች እንደሚካሄድባቸውም ነው የገለጹት። የጳጉሜን ቀናት የአዲሱ ዓመት እቅዶች ይኾናሉም ነው ያሉት።

በየደረጃው ያሉ መሪዎች ጳጉሜን በተገቢው መንገድ እንዲያከብሩም አሳስበዋል። በቀጣይ ዓመት የተሻሉ ሥራዎችን ለመሥራት መዘጋጀት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተረሳችው ገነት”
Next article“በ2016 ዓ.ም የሰላም አየር የምንተነፍስበት እና የምሕረት ዓመት ይኾን ዘንድ ከጳጉሜ 3 እስከ 5 ብሔራዊ የጸሎትና የንስሓ መርሐ ግብር ታውጇል።” የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ