“በትንሹ መጀመር፤ በፍጥነት መማር እና ማስፋት የትምህርት ሚኒስቴር የአሠራር መርህ ነው” ዶክተር ሰሎሞን አብርሃ

59

ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፈው ግንቦት አጋማሽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ ዓዋጅን ማጽደቁን ተከትሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ቀዳሚው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ኾኗል፡፡

አካዳሚያዊ እና ተቋማዊ ነጻነትን ያጎናጽፋል የተባለለትን ራስ ገዝነት በሁሉም የመጀመሪያ ትውልድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመተግበር እየተሠራ ነውም ተብሏል፡፡

ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት የትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከታየው የትምህርት ተደራሽነት አዎንታዊ ክስተት መሳ ለመሳ የትምህርት ጥራቱ መድከም እና ማሽቆልቆል በዘርፉ የታየ ሥጋት እና ቁጭት ሆኾኖ ቆይቷል፡፡

ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስተዋለውን የትምህርት ጥራት ጉድለት እና ምክንያት በጥናት ለማየት ተሞክሯል ያሉት በትምህርት ሚኒስቴር የአሥተዳደር እና መሰረተ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰሎሞን አብርሃ (ዶ.ር) ናቸው፡፡

በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ለተስተዋሉት የትምህርት ጥራት መጓደል በርካታ ችግሮች ነበሩ ያሉት ዶክተር ሰሎሞን የትምህርት ተቋማቱ አሥተዳደራዊ እና አካዳሚያዊ ነጻነት መጓደል አንዱ ችግር ነበር ብለዋል፡፡

በየደረጃው ያሉ የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና አጋር አካላት በጋራ እየሠሩ ነው ተብሏል፡፡ ከጥናቱ ማግስት የተዘጋጀው የትምህርት ፍኖተ ካርታ እና የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ አንዱ እርምጃ እንደኾነም ዶክተር ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ ተቋማዊ እና አካዳሚያዊ ነጻነትን መስጠት የትምህርት ጥራትን ለማምጣት አስፈላጊ መኾኑ ታምኖበታል ያሉት ዶክተር ሰሎሞን በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ በደረጃ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ እርምጃዎች እየተተገበሩ ነው ብለዋል፡፡

ባለፈው ግንቦት ወር አጋማሽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ ዓዋጅን ማጽደቁን ተከትሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ቀዳሚው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ኾኗል ነው ያሉት፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ መኾን ከፖለቲካዊ እና ልማዳዊ ጣልቃ ገብነቶች ተላቀው አካዳሚያዊ እና ተቋማዊ ነጻነት ይሰጣቸዋል ብለዋል ዶክተር ሰሎሞን።

በቅርቡ የትምህርት ሚኒስቴር ቡድን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተመልክቷል ያሉት የአሥተዳደር እና መሰረተ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አፈጻጸም እየተማርን እንሠራለን ነው ያሉት፡፡

“በትንሹ መጀመር፤ በፍጥነት መማር እና ማስፋት የትምህርት ሚኒስቴር የአሠራር መርህ ነው” ያሉት ሥራ አስፈጻሚው ብቁ የሰው ኃይል፣ በጀት፣ ልምድ እና አሠራሮችን እየቀመርን ቢያንስ በሀገሪቱ የሚገኙትን ስምንት የመጀመሪያው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናዎኑ ነው ብለዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱም ራሳቸውን እያዘጋጁ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ስድስቱን የጳጉሜ ቀናት የተቸገረን በማሰብ ፣ በደልን ይቅር በማለት፣ በጾምና በጸሎት ማሳለፍ ይገባል” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
Next article“የተረሳችው ገነት”