
አዲስ አበባ: ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በጳጉሜ ቀናት የሚከወኑ መንፈሳዊ ተግባራትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
ቤተ ክርስቲያኗን ወክለው መግለጫው የሰጡት የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጽዕ አቡነ አብርሃም እና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር) ናቸው።
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በመልዕክታቸው መጪው 2016 ዓ.ም የሰላምና የምህረት እንዲሆን ስድስቱን የጳጉሜ ቀናት አምላክን በፆምና በጸሎት በመጠየቅ ፣ በደልን በይቅርታ በማለፍ ፣ የተቸገረንና የታመመን በመጠየቅና በመርዳት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ብጽዕ አቡነ አብርሃምም “ያለንበት ወቅት የፈተና ነው፤ በዚህ ወቅት መጨነቅ ሳይሆን ሃሳብን ለአምላክ ማቅረብ ይገባል ብለዋል። አምላክን በፆም እና በጸሎት ችግራችን ስንጠይቅ መፍትሄ አለው ነው ያሉት። የእምነቱ ተከታዮች የጳጉሜን ስድስት ቀናት በንሰሐ እና በምሕላ እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ ቀናቱን በፆም ና በጸሎት ለማሳለፍ ማወጇንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!