
ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የከተማ ልማት ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኅላፊ ዶክተር አሕመዲን ሙሐመድ ከሚያስተባብሯቸው ተቋማት ጋር የትውውቅ እና በቀጣይ ሥራዎች መመሪያ ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡
ሥራና ሥልጠና ቢሮ፣ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ፣ መሬት ቢሮ፣ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ እና ገቢዎች ቢሮ በክላስተር የሚያስተባብሩት ዶክተር አሕመዲን ከነበረው አሠራር ያስተዋልናቸው እና የተጠለፉ ሦስት ሥርዓቶች አሉ ብለዋል፡፡
መሬት፣ ግብር እና ጊዜ በብልሹ አሠራር ተጠልፈዋል የሚሉት የክላስተር አስተባባሪው ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት በተቋማት መካከል የትብብር እና በጋራ የመሥራት ባሕልን ማሳደግ በእጅጉ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የከተማ ክላስተርን እንደሚመራ የቢሮ ኅላፊ ፈጣን እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን ማዘመን ይገባል ያሉት ዶክተር አሕመዲን “ነባር ችግሮችን ለይተን እንፍታ፤ በተቻለ መንገድ አዳዲስ ችግሮችን ላለመፍጠር በጥንቃቄ እንሥራ” ብለዋል፡፡
በክላስተሩ ውስጥ የሚገኙ ተቋማት ሌብነትን እና ብልሹ አሠራርን በመታገል፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራርን በመዘርጋት እና ቅንጅታዊ አሠራርን በመተግበር ሌብነትን መታገል የቀጣይ ጊዜ ትኩረት መሥክ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር አሕመዲን አሁናዊ ትውውቃችን ባለፉ ችግሮቻችን ላይ ብቻ እንዳናላዝን፤ ይልቁንም የቀጣይ ትኩረት መሥኮችን እንድንለይ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
ሥራ አጥነትን መቀነስ፣ የመሰረተ ልማት እና አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እና የመኖሪያ ቤት እጥረትን በአማራጭ አሠራሮች መፍታት የከተማ ልማት ዘርፍ ክላስተር የቀጣይ ጊዜያት የትኩረት መስኮች እንደኾኑም ዶክተር አሕመዲን አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!