“በአማራ ክልል ያለውን አሉታዊ ድባብ መቀየር የሚያስችል የሥነ ተግባቦት ሥራ ያስፈልጋል” ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

190
Made with LogoLicious Add Your Logo App

ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ “ ጳጉሜን ለኢትዮጵያ” በሚለው ሀገራዊ ንቅናቄ ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ርእሰ መስተዳድሩ በወረኃ ጳጉሜን ክልሉ አሁን ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ሥራዎችን መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻዋ ወር በጳጉሜን ገንቢ መልእክቶችን ለሕዝብ በማድረስ በአማራ ክልል ያለውን አሉታዊ ድባብ መቀየር የሚያስችል የሥነ ተግባቦት ሥራ ማስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ተቋማት ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን ማስተላለፍ እና መልካም ነገር መሥራት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡

“ጳጌሜን ለኢትዮጵያ” ለአማራ ክልል ፋይዳው ታላቅ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ሰላሙ እንዲረጋገጥ፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች እንዲመለሱ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

ሕዝቡ አሁን ካለበት ስሜት ወጥቶ ተስፋ እንዲታየው፣ አውንታዊ አስተሳሰብ እንዲመጣ የማድረግ ሥራ የመሪዎች ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሁሉም አውንታዊ አስተሳሰብ እንዲገነባ መሥራት ይገበዋልም ብለዋል፡፡

በጳጉሜን ወር ሕዝብን ለመልካም ነገር የሚያነሳሳ፣ ተስፋ የሚሰጥ ሃሳብ መስጠት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ሥራዎቹ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታና ሀገራዊ አውዱን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

የሥነ ተግባቦት ሥራ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር የሚያስተሳስር መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡

በእያንዳንዱ የጳጉሜን ቀን ስያሜ ታሳቢ ያደረገ ሥራ መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡ በሀገራዊ ተቋማት ላይ የሚሰጡ ያልተገቡ ውንጀላዎችን ማስተካከል እና ትክክለኛውን ገጽታ ማሳየት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የጽጥታ ተቋማትን ስም ማጠልሸት እና ያልተገባ ስያሜ መስጠት አስፈላጊ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡ የተዛቡ አካሄዶችን በሥነ ተግባቦት ሥራዎች ማስተካለል እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

በእውነት ላይ የጸና ትውልድ ለመገንባት በአግባቡ መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡ ሙያን፣ ሀገርንና ሕዝብ መውደድ፣ በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖርን ማጎልበት የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል፡፡ አብሮነትን የሚንድ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከት አመለካከት በሀገር ላይ መዘራቱን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ ሕዝብን አብሮ እንዲኖር የሚያደርግ ሥራ መስራት ያስልጋል ነው ያሉት፡፡ መጥፎ አካሄዶችን የሚያክምና የሕዝብን አንድነትን የሚሸረሽሩ ሃሳቦችን የሚኮንን ተግባቦት እንደሚያስፍልግም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት የሚያስችል ሥራ መስራት ይገባናል ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ የአብሮነት እሴቶችን የሚያዳብር ስራ መስራት አለብንም ብለዋል፡፡ የአብሮነት እሴቶችን እና ኢትዮጵያዊነትን ከሚጎዱ ንግግሮች መቆጠብ ይገባልም ነው ያሉት፡፡ አሁን ላይ ያለው ችግር የትርክት ውጤት መሆኑን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ ያልተገቡና የተሳሳቱ ትርክቶች ለችግር ማጋለጣቸውን ነው የገለጹት፡፡ ሀሰተኛ ትርክቶችን የመቀልበስ ሥራ ሁልጊዜም መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከጳጉሜን ወር በኋላ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ለሀገር ግንባታ ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረገ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሥነ ልቡና ውቅሩ መሆኑን በግልጽ ማሳየት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መሠረት ላይ የጸና ሕዝብ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የሕዝብን ሥነ ልቡና፣ ታሪክ እና ማንነት ታሳቢ ያደረጉ ሃሳቦችን መቅረጽ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ወደፊት የአማራ ክልልን ችግር ለመፍታት ታላላቅና ሰፋፊ ሥራዎች እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም የጳጉሜን ወር ለመልካም አጋጠሚ መጠቀም እና ሕዝብን በአዲስ ተስፋ ወደ አዲስ ዓመት ማሸጋገር ይገባል ብለዋል፡፡ ወቅቱን ታሳቢ ያደረጉና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎችን እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል 464 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 4 ሺህ 700 አዳዲስ አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማውጣታቸው ተገለጸ።
Next article“ነባር ችግሮችን ለይተን እንፍታ፤ በተቻለ መንገድ አዳዲስ ችግሮችን ላለመፍጠር በጥንቃቄ እንሥራ” ዶክተር አሕመዲን ሙሐመድ