
ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አመራር እና ሠራተኞች የ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2016 ዓ.ም የዕቅድ ትውውቅ አድርገዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በ2015 ዓ.ም በክልሉ ኢንቨስትመንት ላይ በትኩረት ሲሠራ ነበር ብለዋል።
መንግሥት ከፍተኛ ወጭ እያፈሰሰ ወደ ሀገር የሚያስገባቸውን የአልባሳት፣ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የመሳሰሉትን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን መቻሉንም ተናግረዋል። በዘርፉ ከ63 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የክልሉ ነዋሪዎች ቋሚ የሥራ እድል በመፍጠር ሥራ አጥነትን የመቀነስ ተግባሩን ለማገዝ በትኩረት መሠራቱንም አንስተዋል።
የብድር አቅርቦት ማነስ፣ የኃይል አቅርቦት አለመሟላት እና ባለሃብቶች የወሰዱትን መሬት በፍጥነት ወደ ልማት አለማስገባት የ2015 በጀት ዓመት የክልሉ ኢንቨስትመንት ዋና ዋና ውስንነቶች ስለመኾናቸውም ተነስቷል። በ2016 ዓ.ም እነዚህ ችግሮች ተፈትተው ከዘርፉ የላቀ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በቅንጅት ይሠራልም ተብሏል።
ቢሮ ኀላፊው በ2016 ዓ.ም ወደ አማራ ክልል የሚመጡ የአዳዲስ ኢንቨስተሮችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ ስለመኾኑም በመድረኩ ላይ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስም 464 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 4 ሺህ 700 አዳዲስ አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማውጣታቸውን ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። ፈቃድ ካወጡ መካከል 1 ሺህ 222 የሚኾኑት ያቀረቡት የፕሮጀክት ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ መሬት ተረክበዋል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግም በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል። ለዚህም 826 አዳዲስ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። ከነዚህ ውስጥ 322 ያህሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ናቸው ብለዋል።
በተለይም መሬት ወስደው አጥረው የሚያስቀምጡ እና ለሌላ ዓላማ በሚያውሉ ባለሃብቶች ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ የመሬት ሃብት በአግባቡ እንዲለማ በትኩረት ይሠራል ብለዋል አቶ እንድሪስ።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!