
ጥር 6/1811 ዓ.ም ልክ በዛሬዋ ዕለት! ጀግናው የአንድነት አባት አጼ ቴዎድሮስ ተወለዱ፡፡
‹ሃገሩን ሊያስከብር ጠላት ድል ሊነሳ፣
በወርኃ ጥር ተወለደ ካሳ፡፡›
ኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ ስጋ ሊቀራመቱ እንቅልፍ ያጡት የዓለም ሃገራት ዳር ድንበሯን እሳት ይዘው ከበዋታል፡፡ በወቅቱም በምድሯ ጠንካራ ንጉሥ ጠፍቶ መሳፍንትና መኳንንቱ ሃገሪቷን በመደብ በመደብ ተከፋፍለው ይዘዋት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የማያባራ ጦርነት፣ የከፋ በደልና ግፍም ይፈጸም ነበር፡፡ ጥሮ፣ ግሮ አዳሪው ጭሰኛ የደረሰ መሳፍንት ሁሉ ሀብቱን እየመዘበረበት በድህነትና በችግር መኖር ጀመሯል፡፡
ሁሉም እርስ በርስ ከመጠቃቃትና የራሱን ግዛት ከማስፋፋት የዘለለ በተግባር የተተረጎመ ህልም አልነበረውም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የነገሥታት ኃይል ደክሞ መሳፍንት በገነኑበት፣ የውጭ ጠላቶች በተለይም ቱርክና ግብጽ ኢትዮጵያን ለመዋጥ በቋመጡበት በዚያ ዘመን ነው፤ ዘሩ ከቋራና ከደንቢያ ባላባቶች የሚመዘዝ አንድ ህጻን በቋራ ሻርጌ የተወለደው፡፡ በወርሃ ጥር በስድስተኛው ቀን በ1811 ዓ.ም፤ ልክ በዛሬዋ ዕለት፡፡ የአባታቸው ዘር ከቋራ ባላባቶች ነው፤ ስማቸውም ደጅ አዝማች ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ይባላል፡፡ እናት ደግሞ ከደንቢያ ባላባት፣ ዘራቸው ከቀደሙት የጎንደር ነገሥታት እንደሆነ የሚነገርላቸው እመቴ አትጠገብ ወንድወሰን (የወንድወሰን) ይባላሉ፡፡ እመቴ አትጠገብ ልጃቸው ሃገሩን የሚያኮራ፣ ለበደሏም ካሳ የሚከፍል መልካም ሰው እንደሆነ ስላወቁ ይመስላል ‹‹ካሳ›› ብለው ስም ያወጡለት፡፡ ‹‹ስምንም መልዓክ ያወጣዋል›› እንዲሉ የዘመኑ መካሻ የመልካም ስርዓት መነሻ ሆነ፡፡ የዚያ ዘመን ፍጻሜ፣ የኢትዮጵያ የአዲስ ምዕራፍ ጀማሪ ያ! ህጻን እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በቤተክህነት ተማረ፡፡ ፊደል ቆጠረ፣ ዳዊት ደገመ፣ በመጻሕፍትም ላይ ተመራመረ፡፡ በዚህ ጊዜም ግዕዝ፣ አማርኛና የአረብኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ ቻለ፡፡ ካሳ ከሃይማኖታዊ ትምህርቱ በተጨማሪ የአስተዳደር ስርዓትንም ይማር ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ምድር የሚወርደውን ግፍ ሲያይ አደገ፤ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ስጋት ላይ መውደቅም አሳሰበው፡፡ ታላቅ ራዕይም ሰነቀ፡፡ ልጅ ካሳ ፈረስ ግልቢያ አዋቂ፣ የጦር ፊት አውራሪ፣ የጠላትን ምሽግ ሰባሪ እንደነበረም ይነገርለታል፡፡ አባቱ በልጅነት ስለሞቱ የልጅነት እድሜውን ከአጎቱ ከደጃች ክንፈ ጋር ነበር ያሳለፈው፡፡ በዚህ ጊዜም በጠላት ወገን ሁሉ ያስወደሱት የጦር ሜዳ ገድሎችን ፈጽሟል፡፡ ከደጃች ክንፈ ጋር ተጋጭቶ ወደ ጎጃም በመሻገር ከጎሹ ጋር አስደናቂ ገድሎችን ፈጽሟል፡፡ ለዚህም ነው
‹‹እንኳን ሀበሻ ባለቤትየው፣
ጠላትም ቀና አንድ ቀን ባየው›› የተባለለት፡፡
ከዚያም ወደ ቋራ ተመልሶ የራሱን ጦር ማደራጀት ጀመረ፡፡ በአጭር ጊዜም ቋራን ተቆጣጠረ፡፡ በወቅቱ የውጭ ወራሪ ጦር በመተማ አድርጎ ኢትዮጵያን እየወጋ ነበር፡፡ ተዋበች እንደተማረከች ለካሳ ተነገረው፡፡ ፈረሱን አዙሮ ሱዳን ውስጥ ስናር ወደ ተባለ የጦሩ ስፍራ ገሰገሰ፡፡ በስናርም ያን የጠላት ጦር እንዳልነበር አድርጎ ተዋበችን ከነክብሯ አስመለሰ፡፡ ወደ ቤተ መንግስትም መለሳት፡፡ ቋራንም እስከደንቢያ ድረስ ተቆጣጠረ፡፡
እቴጌ መነንም ያን አመለኛ ልጅ በጋብቻ ካልሆነ በሌላ እንደማይመልሱት ስላወቁ ተዋበችን ዳሩለት፡፡ ተዋበችና ልጅ ካሳ ፍቅር የጀመሩት ካሳ ከስናር ሲመልሳት እንደሆነም ይነገራል፡፡ ተዋበችም በጀግንነቱ ትደመም ነበርና የልቧን መሻት አገኘች፡፡ ብርታትም ሆነችው፡፡ በጋብቻው ወቅትም ደጅ አዝማች ተብሎ በራሱ እጅ ይዞት የነበረውን ግዛት ተሰጠው፡፡ ህልሙን ሳያሳካ የማይተኛው ደጅ አዝማች ካሳም ከብርቱዋ ባለቤቱ ጋር ሆኖ ነገሥታቱን መነንና አጼ ዮሀንስን ጨምሮ መሳፍንቶችን አሸንፎ ግዛቱን አሰፋ፡፡ ልብ ይበሉ! በዚህ ጉዞው ልበ ሙሉው ገብሬ፣ አባ ደፋር ገልሞ፣ አይደፈር አለሜ፣ እንግዳና ሌሎች ታማኝ ሰዎች ነበሩት፡፡ ጠንካራ ገዢ አጥታ የነበረችውን ኢትዮጵያንም አንድ ንጉሥ ብቻ እንዲኖራት አደረገ፡፡ ያ! ጀግናው ደጃች ካሳ በወርኃ የካቲት በሰባተኛው ቀን በ1847 ዓ.ም በተወለደ በ36 ዓመቱ በአቡነ ሰላማ እጅ ቅብዓ ንግሥናን ተቀብቶ በደረስጌ ማሪያም ዘውድ ጫነ፡፡ ስሙም አፄ ቴዎድሮስ ተባለ፡፡ ይህ ስምም ትንቢት የተነገረለት እንደሆነ ስለሚያውቅ ነበር የመረጠው፡፡ ቴዎድሮስ እንደነገሰ እሳት ለኩሶ ኢትዮጵያን ሊያቀጣጥል ሲያሰፈስፍ የነበረው ጠላት ሁሉ አይኑ ጨለማ እግሩ ቄጠማ ሆነበት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አፈር የሚያስግጥ ጀግናው ልጇ ነግሷልና ነው፡፡
ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን እስራኤልንም ከግብጽ ባርነት ለማውጣት አስቀድሞ እቅድ ነድፎ የነበረ ሩቅ አሳቢ ነበር፡፡ ይህን ኃያል ሰው ዶክተር ሄነሪ ብላንክ ‹‹የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ አባት›› ይሉታል፡፡ ኢትዮጵያዊው ደራሲ አቤ ጉበኛ ደግሞ ‹‹ ቴዎድሮስ ገና ገና ወደፊት በሚመጣው የኢትዮጵያ ትውልድ ልብ ውስጥ እንደ እንቁ ያበራሉ፡፡ ቴዎድሮስ የአንድ ትውልድ ብቻ ንጉሠ ነገሥት አይደሉም፡፡ ቴዎድሮስ የዛሬውንና የወደ ፊቱን የኢትዮጵያ ትውልድ በመንፈስ ይገዙታል፡፡ በዚያ ዘመን ከነበረው ትውልድ የቀደመ መንፈስ ነበራቸው›› ብለዋል፡፡ ስለ መይሳው ብዙ ብዙ ተብሏል፤ገና ይባላልም፡፡ አፄ ቴዎድሮስ በዛሬዋ እለት ነበር የተወለዱት፡፡ ትውልዱ ምን ይማር? የአስተያየት መስጫው ለእርሶ ሃሳብ ክፍት ነው፡፡
ምንጭ፡- ጳውሎስ ኞኞ፡- ዓፄ ቴዎድሮስ፣ ተክለፃዲቅ መኩሪያ፡- የኢትዮጵያ ታሪክ ከዓፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መጽሐፍት
በታርቆ ክንዴ
