ዳግም ራስ ገዙ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ!

74

ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ዕውቀት እና ትምህርት ዘመንን የተሻገረ ልምድ ያካበተች ጥንታዊ ሀገር ብትኾንም በዘመናዊ ትምህርት ልምምድ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ የተሻገረ አሻራ እና ልምድ አልነበራትም፡፡

በተለይም ምዕራብ ዘመሙ የዘመናዊ ትምህርት አሻራ በኢትዮጵያ መሰረት የተጣለበት ጊዜ ከሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ ዘመን በኋላ እንደነበር ይነገራል፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓት ወርዶ በሌላ ሥርዓት ሲተካ የተለያየ መልክ እና ቅርጽ የሚፈራረቁበት የሀገሪቷ ዘመናዊ ትምህርት በየዘመኑ በርካታ ውጣ ውረዶችን እና ለውጦችን አስተናግዷል፡፡

ሀገሪቱን ለግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ በዘውዳዊ ሥርዓት የመሩት እና የመጨረሻው ንጉሳዊ መሪ የነበሩት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመናዊ ትምህርት በሀገሪቱ እንዲስፋፋ ያሳረፉት በጎ ተፅዕኖ ዘመን ተሻጋሪ የሚባል ነበር፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ማስፋፋት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ግንባታ ድረስ የንጉሡ ተራማጅ ዕይታ አያሌ ለውጦችን አሳይቷል፡፡ በሀገሪቱ የመጀመሪያው የኾነው እና አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስማቸው ይጠራ የነበረ ፈር ቀዳጅ ታላቅ መካነ-አዕምሮ ኾኖም ይጠቀሳል፡፡

ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲነት፤ ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲነት እስከ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲነት የተሸጋገረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኀበራዊ እና ድኀረ ዘመናዊ ትሩፋቶች ተፅዕኖው የጎላ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡ 1942 ዓ.ም ገደማ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት እርሾ የጀመረው ታላቁ መካነ-አዕምሮ ከአለማያ እስከ ጎንደር እና ሌሎች ኮሌጆችን እያካተተ ተደራሽነቱን ማስፋት ጀመረ፡፡

ከነገረ-መለኮት እስከ ሌሎች ኮሌጆች በአንድ ላይ ተካትተው 1953 ዓ.ም ገደማ የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በመባል የሀገሪቱ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ ኾኖ ተመሰረተ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም በታኅሣሡ ግርግር ወቅት በርካታ መኳንቶቻቸው ያለቁበትን የገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት አዲስ ለተቋቋመው ታላቅ መካነ-አዕምሮ በስጦታ አበረከቱለት፡፡ ውስጣዊ ችግሮቿን እና ፖለቲካዊ ወከባዎቿን በቤተ-ክህነት ሊቃውንት ዙሪያ መክራ እና ዘክራ የምትፈታው ኢትዮጵያም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ፖለቲካዊ ስብራቶቿን እና ማኀበራዊ ሳንካዎቿን የምትጠግንበትን ታላቅ የምሁራን ተቋም አቋቋመች፡፡

ዘውዳዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አክትሞ ዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደር ሲተዋወቅ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ስያሜም ተቀየረ፡፡ አብዮቱ ፈንድቶ ደርግ ወደ መንበረ ሥልጣኑ ሲመጣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲም ስያሜ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ኾነ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን አሁንም ድረስ መጠሪያው ኾኖ የዘለቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስያሜነት ተሰጠው፡፡ ዮኒቨርሲቲው ሥርዓት በተለወጠ ቁጥር ስያሜ ብቻ ሳይኾን ህልውናውን የተፈታተኑ ችግሮችን እና የብርሃን ዘመናትንም አፈራርቆ አሳልፏል፡፡

የንጉሠ ነገሥቱ የመሪነት ዘመን አክትሞ ደርግ ወደ ሥልጣን እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የበላይ ጠባቂ ወይም ቻንስለር ደግሞ የሀገሪቱ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ፡፡ ከንጉሠ ነገሥቱ በማስከተል ከመኳንንቱ እና ከሚኒስትሮቻቸው የተውጣጣ ቦርድ ተቋቁሞም ይሰራ ነበር፡፡ ከቦርዱ ዝቅ ብሎ ደግሞ ከዩኒቨርሲቲው የሚመረጡ ፋካሊቲ ካውንስሎች ነበሩት፡፡ የፋካሊቲ ካውንስሉ በኋላ ላይ ሴኔት ወደ ሚል ስያሜ መለወጡ ይገራል፡፡

የኋላ ኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ሥር እንዲተዳደር መደረጉን ተከትሎ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበረውን አንጻራዊ የአካዳሚክ ነጻነት ተነጥቆ ነበር ያሉን በትምህርት ሚኒስትር የአሥተዳደር እና መሰረተ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰሎሞን አብርሃ (ዶ.ር) ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲውን የአካዳሚክ ነጻነት ማጣትን ተከትሎ በትምህርት ጥራት ላይ የነበረው ተጽዕኖ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ አሁን ላይም የትምህርት ጥራትን ችግር ለመቅረፍ ትምህርት ሚኒስትር ከወሰዳቸው ማሻሻያዎች አንዱ ተቋማዊ ነጻነትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል ዶክተር ሰሎሞን፡፡

ባለፈው ግንቦት አጋማሽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ለማቋቋም የሚያስችል አዲስ ዓዋጅ አጽድቋል፡፡ በዓዋጁ መሰረት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የሀገሪቱ ቀዳሚ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ኾኗል ያሉት ዶክተር ሰሎሞን ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሥልጣን እና ነጻነት አግኝቷል ብለዋል፡፡ አካዳሚያዊ ነጻነት እና ተቋማዊ ነጻነት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲተ አዲስ አይደለም የሚሉት የትምህርት ሚኒስትር የአሥተዳደር እና መሰረተ ልማት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቻንስለር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም እንደነበሩ አይዘነጋም ነው ያሉት፡፡

ዶክተር ሰሎሞን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ መኾኑ አሥተዳደራዊ ነጻነት፣ ነጻና ተጠያቂ የፋይናንስ ሥርዓት፣ የሰው ኃብት አሥተዳደር ፣ ነጻነት እና ከምንም በላይ የአካዳሚክ ነጻነት ስለሚሰጠው በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚስተዋለውን የትምህርት ጥራት ጉድለት ለማረም የሚያስችል እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በራስ ገዝ አሥተዳደር ውስጥ የሚገኘው ነጻነት ደግሞ በተቋማዊ፣ በአሥተዳደራዊ እና በአካዳሚክ ነጻነት የሚገለጽ ነው ተብሏል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው ኾኗል ሲባል ከፖለቲካዊም ኾነ ልማዳዊ ጣልቃገብነት ነጻ ኾኗል ማለት ነው የሚሉት ዶክተር ሰሎሞን አካዳሚያዊ ነጻነት የማሰብ ነጻነትን የሚሰጥ መርህ መኾኑ ዋና ጉዳይ ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት፡፡ ራስ ገዝ ስንል ምን ማስተማር እንዳለበት፣ የትኛውን ካሪኩለም መቅረጽ እንዳለበት፣ መክፈት የሚፈልገውን ትምህርት ክፍል የመወሰን፣ የጥናትና ምርምር ዘርፎችን መወሰን እና ራሱን በሰው ኃይል ለማደራጀት የማንም ጣልቃገብነት እንዳይኖር ነጻነትን ከተጠያቂነት ጋር መስጠት ማለት መኾኑን ዶክተር ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአገልጋይነት ቀን ጳጉሜን 1 በሁሉም የሀገሪቱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደሚከበር ተገለጸ።
Next article“መነጋገር መወያየት ለሀገር አንድነት ያለዉ ድርሻ የላቀ በመኾኑ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚዘጋጀዉ ስለ ኢትዮጵያ መድረክ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ከንቲባ አዳነች አቤቤ