
አዲስ አበባ: ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የአገልጋይነት ቀን ጳጉሜን 1 በሁሉም የሀገሪቱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደሚከበር የጤና ሚኒስቴር ፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።
በተለይም ለሰፊው የማኅበረሰብ ክፍል አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚ ከኾኑ ዘርፎች መካከል የትራንስፖርት ፣ የሲቪል ሰርቪስ እና የጤናው ዘርፍ ተጠቃሾች ናቸው።
ተቋማቱ በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጣቸው ማኅበረሰቡን ማርካት ባለመቻላቸው በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚነሳባቸው እንደመኾኑ ጷጉሜን 1 የሚከበረውን የአገልጋይነት ቀን ምክንያት አድርገው የሕዝቡን የአገልግሎት እርካታ ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ ነው በመሥሪያ ቤቶቹ መግለጫ ላይ የተብራራው።
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ.ር) ኢትዮጵያን እናገልግል በሚል መሪ መልእክት ጳጉሜን 1 የሚከበረው የአገልጋይነት ቀን በትራንስፖርት ዘርፉ ከንጋቱ 11:30 ጀምሮ በትራንስፖርትና ሎጅስቲክ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሚመሰገኑበት ፤ ክፍተቶች የሚለዩበት ይኾናል ብለዋል።
በእለቱ ትራንስፖርት የሚሰጡ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች በነፃ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግም አስገንዝበዋል።
የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ.ር) በቅንነትና በታማኝነት እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ከፍለው ሙያቸውን በአግባቡ እየተወጡ ላሉ የጤና ባለሙያዎች በእለቱ ዕውቅና የሚሰጥበት ፤ 200 ሺህ ለሚኾኑ ታካሚዎች በጤና ተቋማት ነፃ ሕክምና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጥበት እንደሚኾን ገልጸዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ 38 ዓመትና ከዛ በላይ በቅንነት ያገለገሉ የመንግሥት ሠራተኞች በእለቱ ዕውቅና ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!