
ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ ከተማ ተጀምሯል።
ጉባኤው የሚከናወነው “አረንጓዴ መር ዕድገት እና የአየር ንብረት ፋይናንስ መፍትሔ ለአፍሪካና ለዓለም” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
በኬንያ መንግሥት አዘጋጅነት የሚካሄደው ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ እና ከለውጡ ጋር የመጡ ጉዳቶች በዓለም ላይ በተለይም በአፍሪካ እያደረሱት ላለው ተጽዕኖ አፋጣኝ መፍትሔ ማበጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክር ኢዜአ የአፍሪካ ኅብረትን ጠቅሶ ዘግቧል ።
ጉባኤው የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችሉ አማራጮችን በማቅረብ የተግባር ዕቅድ የሚያዘጋጁበት፤ በዚህም “የናይሮቢ ድንጋጌ” ለማርቀቅ መደላድል መፍጠር እንደሚያስችል ገልጿል።
ከሕዳር 20 እስከ ታኅሣሥ 2/2016 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ ከሚከናወነው 28ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) በፊት አፍሪካ በጉባኤው ላይ የጋራ ድምጽ ማሰማት በምትችልበት ሁኔታ ላይም እንደሚመክር ይጠበቃል።
የአፍሪካ ሀገራት እ.አ.አ በ2016 በፓሪስ በተካሄደው 21ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP21) የተቀመጡ ግቦችን ከማሳካት አኳያ ያሉበት ደረጃ እንደሚገመገምም ተመላክቷል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት “የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት” በሚል መሪ ሀሳብ የተለያዩ መርሐ-ግብሮች እንደሚከናወኑ ሕብረቱ ገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!