“በጋራ እንጠቀም ስንል ለእኛም ይበጃል፣ ለእነርሱም ይበቃል”

45

ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጥበብ፣ የታሪክ፣ የአንድነትና የታላቅነት መገለጫ የኾነው ግዮን (ዓባይ) ከኢትዮጵያ አብራክ መንጭቶ ለዘመናት ፈስሷል፡፡ እረኞች በዋሽንት እያጀቡት፣ በዜማ እየሸኙት የእናቱን አፈር እየቆረሰ፣ ከእናቱ ርቆ በረሃ የበዛባቸውን ሀገራት እያረሰረሰ ኖሯል፡፡ ዓባይ በሀገሩ ማደሪያ አጥቶ ለዘመናት በትካዜ ተጉዟል፡፡ የእናቱን አፈርም ያለ ማቋረጥ አግዟል፡፡ በየዘመናቱ የነገሡ የኢትዮጵያ ነገሥታት ተጓዡና ተካዡን ወንዝ በሀገሩ ያስቀሩ ዘንድ ውጥን ወጥነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ነገሥታት ዓባይን ይገድቡ ዘንድ በተነሱ ቁጥር የግብጽ ነገሥታት የእጅ መንሻ እየያዙ ዓባይን ይተውላቸው ዘንድ ተማጽነዋል፡፡ እጅ መንሻ እየያዙ ከኢትዮጵያ ነገሥታት ደጅ ወድቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ነገሥታት አቅማቸው የደከመ በመሰላቸው ዘመን ደግሞ ዓባይን ከእነ ምንጩ እንወስደዋለን እያሉ ዝተዋል፤ ይወስዱት ዘንድም ሞክረዋል፡፡ ዛቻቸው እና የጦር ነጋሪታቸው ግን አንድ ጊዜም አልሠራም፡፡ በብርቱ ኢትዮጵያውያን ድል ተመትተው ተመለሱ እንጂ፡፡ ባይኾን የእጅ መንሻው ተሽሏቸዋል፡፡ ዓባይም የእናቱን አፈር እየቆረሰ የሚጓዝባቸውን ሀገራት ምድር እያረሰረሰ ኖሯል፡፡ ከዘመናት በኋላ ኢትዮጵያ ዓባይን በዋሽንት እያጀበች፣ ዜማ እያዜመች ከመሸኘት ወጥታ ትጠቀምበት ዘንድ ወደደች፡፡ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብንም ጉባ ላይ ጀመረች፡፡

በቀደመው ዘመን ጀምሮ ዓባይን እንዲነኩባት የማትሻው ግብጽ የዓባይ ግድብ ከመታሰቡ ጀምሮ አይኾንም ፣ አይደረግም አለች፡፡ እንዳይጀመርም የተቻላትን አደረገች፡፡ ኢትዮጵያ ግን ግድብ ጀመረች፡፡ ግብጽ የግድቡ ሂደትም አይቀጥልም አለች፡፡ ኢትዮጵያ ግን በልጆቿ እውቀት፣ ሃብትና ጉልበት ግድቡን ቀጠለች፡፡

የዓባይ ጉዳይ ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ አልፎ የአፍሪካ፣ የአረብ ሊግ እና የመላው ዓለም መነጋገሪያ ኾነ፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽም በዓባይ ጉዳይ ያላቸውን ልዩነት ለመፍታት ብዙ ጊዜ ውይይት እና ድርድር አደረጉ፡፡ ድርድራቸው በብዙ መንገድ ቢያቀራርባቸውም አሁንም ሁሉንም የሚያስማማ ስምምነት ላይ ግን አልደረሱም፡፡

በአንድ ወቅት የሦስቱ ሀገራት ድርድር እና የሌሎች ጣልቃ ገብነት ከፍ ብሎም መነገር ጀምሮ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ግን በብልህ ልጆቿና በክፉ ቀን አጋሮቿ የሌሎችን ጣልቃ ገብነት እያመከነች ቆይታለች፡፡ ችግሩን በአፍሪካ ጥላ ስር ብቻ ይፈታል በሚለው አቋሟ ጸንታለች፡፡ በመካከል ተቋርጦ የነበረው የሦስቱ ሀገራት የዓባይ ጉዳይ ድርድር በቅርቡ ዳግም ጀምረዋል፡፡ ይህም ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም አስከብሮ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ግብጾች ለድርድር የሚቀርቡት ሲሸነፉ ነው ይላሉ፡፡ ከድርድር በፊት የሚያዩዋቸው እና አቅደው ያልተሳኩላቸው፣ የማይሳኩላቸው በርካታ ጉዳዮች እንደነበሩም ነው የሚናገሩት፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡን መገደብ ብቻ ሳይኾን የመጠበቅ ግዴታም አለባት የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው ኢትዮጵያውያንን በወንዛቸው ማንም ኃይል አትጠቀሙ ሊል አይቻለውም፣ ቢልም አይሳካለትም ብለዋል፡፡ ግብጾች ዓባይን (ናይልን) በተመለለከተ በርካታ ኮንፈረንሶችን፣ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያን ይነካል ነው የሚሉት ፕሮፌሰር አደም፡፡ በግድቡና በኢትዮጵያ ላይ የሚሠሩት ፕሮፓጋንዳ ከፍተኛ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያን በሚገባት ልክ ማሳየት ይገባል ነው ያሉት፡፡ እንደ ታሪክ ተመራማሪው ገለጻ የግብጽ እናት ለልጇ ጡት ስትሰጥ ወተት ብቻ ሳይኾን የናይልን ታሪክም ለልጇ ትነግረዋች፡፡ ይህ ወተት የተገኘው ከናይል ነው፣ ናይልን ካጣህ ወተትም አታገኘም ትለዋለች፡፡ የግብጽ ልጆች ወታደራዊ ስልጠና ወስደው ሲመረቁ ለናይል እሞታለሁ ብለው ቃለ መሃል እንደሚፈጽሙም ገልጸዋል፡፡ ግብጾች ዓባይን የሚመለከቱት ከፈጣሪ የመጣ፣ ለእኛ ብቻ የተሰጠ ነው በማለት ነው፡፡

ግብጽ በሕዳሴው ግድብ የመጀመሪያዎቹ የግንባታ ዓመታት ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ልትገነባው አትችልም የሚል እምነት እንደነበራቸውም አስታውሰዋል፡፡ ጩኸቱ የበዛው እውን እየኾነ ሲመጣ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሕዳሴውን እየገነባች ስትቀጥል ግብጽ ወደ አረብ ሊግ ከዚያም ወደ ጸጥታው ምክር ቤት የግድቡን ጉዳይ ይዛ በተደጋጋሚ መሰየሟንም ተናግረዋል፡፡

በቀድሞው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ ዘመን የሕዳሴ ግድቡ ይመታ የሚል ሀሳብ ተነስቶ እንደነበር ያስታወሱት የታሪክ ተመራማሪው ያ ዓላማና ዒላማ ግን ሳይሳካ በሃሰብ ብቻ ቀረ ይላሉ፡፡ በጸጥታ ምክር ቤት ግብጽ ባላሰበችውና ባልጠበቀችው መንገድ እንደከሸፈባትም አስታውሰዋል፡፡ ከብዙ ክርክር በኋላ ጉዳዪ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር እንዲካሄድ መደረጉንም ያነሳሉ፡፡ ግብጽ ግን ከአፍሪካዊነቷ ይልቅ አረብነቷ የሚያመዝንባት፣ አፍሪካዊነቷን ጥላ የምትንቀሳቀስ ሀገር መኾኗን ነው የሚያነሱት፡፡ ግብጽ ከጀርባ የወጠነቻቸው ውጥኖች አልሳካ ሲሏት አማራጭ አጥታ ወደ ድርድር መምጣቷንም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ፈጣሪ እያገዛት የውኃ ሙሌቷን ማከናወኗን እና እያከናወነች መኾኗን ነው የገለጹት፡፡ አሁን የሕዳሴው ግድብ ራሱን ጠባቂ ኾኗል፡፡ አሁን ግብጽ የሕዳሴ ግድቡ ላይ አንዳች ጥቃት ላስብ ብትል በራሷ ላይ ሞት እንደ መደገስ ይቆጠራል ይላሉ፡፡ የሕዳሴው ግድብ የተቀበረ ፈንጅ ማለት ነው፤ አሁን ላይ ራሱን የሚከላከልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ነው ያሉኝ፡፡

ወደ ድርድር ሲመጣ ኢትዮጵያ ጠንካራ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋታል የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው በሳል ዲፕሎማትንም ትሻለች፡፡ ኢትዮጵያ በጋራ እንጠቀም እንጂ ብቻዬን ልጠቀም አላለችም፤ በጋራ እንጠቀም ስንል ለእኛም ይበጃል፣ ለእነርሱም ይበቃል ነው ያሉት፡፡
ግብጽ በተደጋጋሚ የምታነሳቸው የታሪክ ስምምነቶች ኢትዮጵያን አይወክሉም፤ አይመለከቱም፡፡ ምክንያቱም ባልነበረችበት ስምምነት ለድርድር አትቀመጥም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሌለችበት ስምምነት አትገዛም፣ ግብጽ አሁንም ያንን ስምምነት አስታውሳ ከመጣች ድርድሩ ዋጋ አይኖረውም ነው የሚሉት ፕሮፌሰር አደም፡፡

ችግሮችን በድርድር መፍታት እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር መጣላቱ አይበጅም የሚሉ የግብጽ ምሁራን መምጣታቸውን ያነሱት የታሪክ ተመራማሪው ኢትዮጵያ ከፈለገች ዓባይን የሚመግቡ ወንዞችን አቅጣጫቸውን ቀይራ ዓባይን ማደኅየት ትችላለች እያሉ ነውም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሃብት እያላት ሁልጊዜም ተርባ መኖር የለባትም፣ በሃብቷ መጠቀም አለባት፡፡ ለዚህ ደግሞ ልጆቿ መሥራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ የዓባይ ድርድር የሰመረ እንዲኾን የሃይማኖት ተቋማትም ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ያነሱት የታሪክ ተመራማሪው የእስልምና ጉባኤ ሙስሊሙ ዓለምን በጎኑ ማድረግ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ከግብጽ ቤተክርስቲያን ጋር ጥብቅ ግንኙነት መፍጠር አለባት ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል የነበረውን ግንኙነት ታሳቢ በማድረግ ድርድሩ መካሄድ አለበትም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ጥቅሟን የሚያስከብር አጀንዳ መንደፍ እንዳለባትና ዲፕሎማሲዋ ጠንካራ መሆን እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያሏትን ጠንካራ ጎኖች ማዳበር እንደሚገባትም ተናግረዋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጸጥታና በሌሎች ችግሮች ፈተና ያልወሰዱ ከ18 ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለመፈተን ዝግጅት ተደርጓል” የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት
Next articleበኩር ጋዜጣ ነሐሴ 29/2015 ዓ.ም ዕትም