“በጸጥታና በሌሎች ችግሮች ፈተና ያልወሰዱ ከ18 ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለመፈተን ዝግጅት ተደርጓል” የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት

44

ባሕር ዳር: ነሐሴ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በፀጥታና በሌሎች ችግሮች ፈተና ያልወሰዱ ከ18 ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለመፈተን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ። በጎንደር፣ በጋምቤላ፣ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች 17 ሺህ 753 ተማሪዎችና በውጭ ሀገራት 300 ተማሪዎች ይፈተናሉ።

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተና ከሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ዙሮች መሰጠቱ ይታወቃል። ሆኖም በአማራ ክልል እና በጋምቤላ ክልል ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሙሉ ለሙሉና በከፊል ፈተና ያልወሰዱ ተማሪዎች መኖራቸውን የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈራ ፈይሳ ገልጸዋል።

በተለይም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሦስት መፈተኛ ጣቢያዎች ሲፈተኑ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል ከ16 ሺህ 580 በላይ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከሁለት እስከ ሦስት የትምህርት ዓይነቶችን ሳይፈተኑ መቅረታቸውን ገልፀዋል። በጋምቤላ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት ደግሞ ከ100 በላይ የማኅበራዊ ሳይንስና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናውን በከፊልና ሙሉ ለሙሉ አልወሰዱም ብለዋል።

በሕግ ጥላ ሥር በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ 982 ተማሪዎችና በኢትዮጵያ ሥርዓተ-ትምህርት በውጭ ሀገራት የሚማሩ 300 ተማሪዎችን ጨምሮ በድምሩ ከ18 ሺህ በላይ በከፊልና ሙሉ በሙሉ ፈተና ያልወሰዱ መሆኑን ገልፀዋል። በመሆኑም በፀጥታ ችግር ያቋረጡትን፣ በማረሚያ ቤት የሚገኙና በውጭ ሀገራት የሚማሩ ተማሪዎች ፈተናውን እንዲወስዱ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለዚህም የፈተና ህትመት፣ የሰው ኃይልና የበጀት ዝግጅት እየደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከየአካባቢው አስተዳደሮች፣ የትምህርት ቢሮዎች፣ ከወላጆችና ከተማሪዎች ጋር ውይይቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል። ተማሪዎች ስነ-ልቦናቸው ለፈተና ዝግጁ ሲሆን እንዲሁም አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ መኖሩን ማረጋገጫ ሲገኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈተኑ አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቁመዋል።

በውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ ሥርዓተ-ትምህርት የሚማሩ 300 ተማሪዎችም ከዛሬ ነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜ 2 ቀን 2015 ዓ.ም የሚፈተኑ ይሆናል። ለዚህም የፈተና ጣቢያ አስተባባሪዎች ከኢትዮጵያ ፈተናው ወደሚሰጥባቸው ሀገራት መጓዛቸውን ነው ያነሱት። እንደ ኢዜአ ዘገባ በፀጥታና ሌሎች ችግሮች ፈተና ያልወሰዱ ተማሪዎች በአፋጣኝ የሚፈተኑበትና ውጤታቸው ሐምሌ ላይ ከተፈተኑ ሁሉም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ጋር ውጤታቸውን ይፋ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ችግሮቿን የመፍታት አቅም አላት” የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል
Next article“በጋራ እንጠቀም ስንል ለእኛም ይበጃል፣ ለእነርሱም ይበቃል”