“ኢትዮጵያ ችግሮቿን የመፍታት አቅም አላት” የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል

89

ባሕር ዳር: ነሐሴ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላማውያን የሚኖሩባት፣ ሰላምም የበዛባት፣ ሰላም ያጡ ሁሉ የሚሸሸጉባት፣ የመከራና የስቃይን ቀን የሚያልፉባት ሀገር ሆና ኖራለች – ኢትዮጵያ!

በሰርክ የፈጣሪ ስም የሚጠራባት፣ ሰላም የኾነ አምላክ የሚመሰገንባት፣ ሰላምና ፍቅር ያድላት ዘንድ የሚለመንባት፣ ጸጋ የበዛላቸው አበው ያሉባት፣ በረከት የማይለያቸው እመው የሚጸልሉባት፣ አምላክም የመረጣት፣ የተዋበውን ሁሉ የሰጣት ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለችበት የመረጋጋት ችግር ስለምን ሰላም አጣች? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።

ኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥትን አስቀድማ ያረቀቀች፣ በጸና ሥርዓተ መንግሥት ዘመናትን የተሻገረች፣ ለዘመናት በዘለቀው መንግሥቷ አያሌ ታሪኮችን የሠራች፣ ዘመናትን በነጻነት የኖረች፣ ቀኝ ገዢዎችን የሰበረች፣ ፍትሕ አዋቂዎችን ያነገሰች፣ ብልኾችን የወለደች፣ መካሪና ዘካሪዎችን ያቀፈች ኢትዮጵያ ስለ ምን ሰላም አጣች? የተጣላን የሚያስታርቁ፣ የፈሰሰን ደም የሚያደርቁ አበው ያልጠፉባት፣ የሽማግሌዎች መቀመጫ ጥላ ያልታጣባት፣ የአምላክ በረከትና ረድኤት ያልተለያቸው አበው ፊታቸውን ያላዞሩባት፣ ተግሳጽና ምክር የሚሰሙ ልጆች ያልነጠፉባት፣ ቃል ኪዳን የሚከበርባት፣ መልካም ንግግር የሚሰማባት፣ ክፉ ንግግር የሚወገዝባት የተባለች ሀገር ናት።

በሠንደቁ አምላክ ሲባል ጥሉን የሚረሳ ሕዝብ ባለባት፣ የአምላክ ስም ሲጠራ ጠብና ክርክር የሚቆምባት፣ ከአንተ በፊት እኔ ልሙትልህ በሚባልባት፣ ታናሽ ታላቁን በሚያከብርባት፣ ትዕዛዙን የሚሰማባት፣ ታላቅ ታናሹን የሚወድባት በተባለች ስሟን በረቀቀ ቀለም ላይ ያኖረች ሀገር ናት። ፍትሕ የሰፈነባት የተባለች፣ የፍትሕ አዋቂዎች ሀገር የተሰኘች፣ በዓለም ታሪክ ፊት የተከበረች፣ የረቀቀና የገዘፈ ታሪክ የከተበች፣ ከድል አድራጊነት ውጭ የሽንፈት ታሪክ በታሪኳ ያላስመዘገበች ኢትዮጵያ ስለምን ሰላም አጣች? በባርነት የነበሩ ሁሉ ነጻ አውጫችን የሚሏት፣ ጥቁሮች ሁሉ የነጻነታችን እናት፣ በጨለመ ዘመን ብርሃን ያየንባት እያሉ የሚጠሯት፣ በስሟ የሚመክቧት፣ በክብሯ የሚከበሩባት፣ የሚኮሩባት ሀገርም ናት። አያሌ ፈተናዎችን በልጆቿ ጥበብ ያለፈች፣ የመከራውን ማዕበል በጽኑ መርከብ የተሻገረች፣ የክፉ ዘመንን ባሕር በብልሃት በትር የከፈለች፣ አትወጣም ከተባለችበት የመከራ ዘመን የወጣች፣ ወደቀች ሲባል ጠላቶቿን ጥላ የተነሳች፣ ደቀቀች ሲባል ይባስ ብላ የጠነከረች፣ አብዝታም የፈረጠመች ኢትዮጵያ ስለ ምን ሰላም አጣች?

የተጣሉትን የሚያስታርቋቸው፣ የተለያዩትን አንድ የሚያደርጓቸው፣ ደም የተቃቡትን ደማቸውን የሚያደርቁላቸው፣ ለግድያ የሚፈላለጉትን በፍቅር የሚያስተምሯቸው ሽማግሌዎች ማሸማገል ትተው ይኾን? ወይንስ የሽማግሌን ቃል የሚሰማ፣ ሽምግልናን የሚያከብር ልጅ ጠፍቶ ይኾን? ለጥል የተነሳውን በሠንደቁ አምላክ ብሎ የሚያቆም ታላቅ ሰው በምድሯ ጠፍቶ ይኾን ወይስ ሠንደቁን የማያከብር ትውልድ ተፈጥሮ ይኾን? ብቻ ግን ኢትዮጵያ ሰላም አጥታለች፡፡ ክብሯን እና ዝናዋን የሚመጥን የልጆቿን ፍቅርና ሰላምም አብዝታ ትፈልጋለች፡፡

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ኢትዮጵያ ለየትኛውም ቀኝ ገዢ ያልተበገረች፣ በልጆቿ አንድነት ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀገር ናት ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ የአውሮፓውያንን የቅኝ ገዢነት ዕቅድ ያመከነች፣ በቅኝ ግዛት ለተያዙ የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌና አርዓያ የኾነች ናት፡፡ ኢትዮጵያ የጥቁሮችን መብት የምታስከበር፣ በነጮች ዘንድ ግርማና ሞገስ የተሰጣት፣ ቅኝ ገዢዎችንም ያንበረከከች፣ የአፍሪካውያን የመብት ተሟጋች ናት ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ብዙ ክብር ያላት ሀገር መኾኗንም ፕሮፌሰር አደም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ውበት አድርገው ክብራቸውን በመጠበቅ ተከባብረው ኖረዋል፤ አሁን ያለው ትውልድ ግን ኢትዮጵያን በትክክል ያውቃታል ወይ ? የሚለው ታላቅ ጥያቄ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ ኢትዮጵያን በትክክል አለማወቅ ለኢትዮጵያ ያልተገባ ሥራን ለመሥራት ይጋብዛልና፡፡

ኢትዮጵያን ባለማወቅ ነው ለድኅነት የተጋለጥነው፣ ኢትዮጵያን ባለማወቅ ነው ችግር የገጠማት፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያን በደንብ እያወቅናት አይደለም ይላሉ የታሪክ ተመራማሪው፡፡ ኢትዮጵያ እንድትታወቅ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች የማንበብ እና የመጻፍ ትምህርት ብቻ ሳይኾኑ ጠለቅ ያለ ጥናት የሚካሄድባቸው ሊኾኑ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያን በትውልዱ ዘንድ እንድትታወቅ ያደርጋታል ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ለተነሳው ችግር ምክንያቱ ኢትዮጵያውያኑ ኢትዮጵያን ባለማወቃቸው ነው ይላሉ፡፡ አዲሱ ትውልድ ሀገሩን በትክክለኛው መንገድ የመረዳት ችግር ገጥሞታል ነው የሚሉት፤ ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለም የሚሉት ፕሮፌሰር አደም ጦርነት ሕይወትና ሀገርን እንደሚያሳጣ ከሌሎች ሀገራት ትምህርት መውሰድ አለብን ብለዋል፡፡ እንደ ታሪክ ተመራማሪው ገለጻ ጦርነት ሲገቡበት በሩ ሰፊ ሲወጡበት ግን በሩ ጠባብ ነው፡፡ ጦርነት ማንንም አይምርም፣ ሁሉንም ያወድማል፣ ሀገር አልባ አድርጎ ያስቀራልም ብለዋል፡፡ ሰላማችንን እያጣን፣ ጦርነት እያስነሳን በሄድን ቁጥር ለዓለም የመሣሪያ ነጋዴዎች የገበያ እድል እየከፈትን እርስ በእርሳችን እየተላለቅን እንሄዳለን ነው ያሉት፡፡ ለረጅም ዓመታት በጦርነት የቆዩ ሀገራት ሕዝቦች አሁን ድረስ ጤናማ አለመኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ሰላም እንዲኖራት የማይፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን መረዳትና የእነርሱን እቅድ ማክሸፍ ይገባልም ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ በቀጠለች ቁጥር ክብሯን እያጣች፣ ታላቅነቷን እየተነጠቀች ትሄዳለችም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዳታገኝ እጃቸውን የሚያስረዝሙ ሀገራት መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ጠላቶች ያሉባት ሀገር መኾኗን በመገንዘብ፣ ሰላም እንዳይደፈርስ በመጠንቀቅ፣ አንድነትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን ኾነን መቆም አለብን ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ችግሮቿን የመፍታት አቅም እንዳላት ያነሱት የታሪክ ተመራማሪው የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት መፍታት ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚው መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ጦርነት ያስከተለውን እና የሚያስከትለውን ጉዳት አውቀነዋል፣ ጦርነት በሀገር እንዳይኖር መሥራት አለብን ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ካጣች የምስራቅ አፍሪካ ሰላም ያጣል፣ የመላው አፍሪካ ሰላምም ይናጋል፣ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለምስራቅ አፍሪካና ለመላው አፍሪካ ሰላም መሆን መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ኢትዮጵያን በውል የሚያውቁ ኢትዮጵያውያን እንደሚያስፈልጓት የተናገሩት ፕሮፌሰር አደም በኢትዮጵያ ምድር እንደ ቀደመው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ትውልድ አይቼ ማለፍን እፈልጋለሁ ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያዊ ሁኑላት፣ ኢትዮጵያም የናፈቀችውን ሰላምና መረጋጋት ስጧት፣ ኢትዮጵያ የሚኖሩባት ብቻ ሳይኾን በደንብ የሚያውቃት እና ስለ እርሷ ክብርና ሰላም የሚኖርላት ትውልድ ትሻለች እና፡፡ ለእርሷ የሚኖር በተገኘ ጊዜ ኢትዮጵያ ሰላማዊት ሀገር ኾና ትኖራለች፣ ብጥብጥና ሁከትን ከምድሯ ታርቃለች፣ ከትክሻዋም ትጥላለች፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቺርቤዋ ናሲ 30/2015 ም.አሜታ እትሜት
Next article“በጸጥታና በሌሎች ችግሮች ፈተና ያልወሰዱ ከ18 ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለመፈተን ዝግጅት ተደርጓል” የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት