ድርድሮች በጥንቃቄ መመራት እንዳለባቸው ምሁራን አሳሰቡ፡፡

387

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዝቅተኛ ውሃ የመልቀቅ መጠን፣ በድርቅና በተራዘመ ድርቅ ወቅት የሚኖረውን ትብብር እንዲሁም የግድቡን የውሃ አሞላል በመለከቱ ጉዳዮች ላይ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ከሰሞኑ ቢመክሩም ያለስምምነት ስብሰባቸውን ቋጭተዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ዘውዱ መንገሻ የግብፅ ሚኒስትሮች አቋም የዓባይ ወንዝ ፍሰት ከአማካይ በታች ከሆነ ያላቸውን ጥቅም ሙሉ ለሙሉ ማስጠበቅን ያስቀደመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የድርቅ ወቅት ሆኖ ውሃው በእጅጉ በሚቀንስበት ጊዜ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ፍላጎትና ጥቅም ይገድባል ነው ያሉት፡፡

ግብጻውያን የግድቡ አሞላል ከ12 እስከ 21 ዓመታት እንዲወስድ የፈለጉበት ምክንያት የተጠቃሚነት መብታቸውን ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ በመሠረታዊነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ዓለም አቀፍ ሀገር ዘለል ወንዞች በተመለከተ ያለው ሕግ ወይም ተስማምተው ተገዢ የሚሆኑበት መርህን ማየት ተገቢ ነው ያሉት አቶ ዘውዱ ስለአጠቃቀሙ በግልጽ የተስማሙበት ስምምነት የለም ብለዋል፡፡

በ1929 እና 1959 (እ.ኤ.አ) የተደረጉት ስምምነቶችም ቢሆኑ ቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ፣ ግብፅና ሱዳንን ብቻ አሳትፋ ድርድር ማድረጓን ነው ያስታወሱት፡፡ በዓለም አቀፍ ሀገር አቋራጭ ወንዞች ሕግ ውሃን በእኩልነትና በፍትሃዊነት መጠቀም እና ውሃን ሲጠቀሙ በሌሎች የተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት አለማድረስ የሚሉ ሁለት መሠረታዊ መርሆዎች እንዳሉ ያስረዱት መምህሩ ውሃን በፍትሃዊነትና በእኩልነት መጠቀም ሲባል ሀገራት ውሃውን በአግባቡ ስለማጋራታቸው ግን ጥያቄ እንደሚነሳ ነው የተናገሩት፡፡

ይህንን በተመለከተ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአውሮፓውያኑ 1997 ወጥቶ በ2014 ወደ ትግበራ የገባ ስምምነት መኖሩን አቶ ዘውዱ ነግረውናል፡፡ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ስምምነቱን ያልተቀበሉ ሀገራት ቢሆኑም ስለፍትሃዊ አጠቃቀም ስናነሳ በተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ ያለው የሕዝብ ቁጥር፣ ከውሃው ያላቸው ድርሻና አስተዋጽኦ፣ ከዚህ በፊት ያገኙት የመጠቀም ዕድል፣ አቅማቸውና ሌሎች ነጥቦች ግንዛቤ ውስጥ ይገባሉ፡፡

እነዚህን ሁሉ ከግምት ውስጥ አስገብተን ስንመለከት ኢትዮጵያ በግብፅ ደረጃ ቀርቶ ምንም የመጠቀም እድል ሳታገኝ በርካታ ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ በሌሎች የተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት ማድረስ አይገባም ቢባልም ግብፅ የዓባይን ወንዝ ከተፋሰሱ ውስጥም ሆነ ውጭ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ድረስ በመዝለቅ ውሃውን ትጠቀምበት ነበር ብለዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ ወንዙን ለመስኖ ወይም ውሃን ለሚያባክን ሥራ ሳይሆን አገልግሎት ላይ የምታውለው ኃይል ለማመንጨት ነው፤ በመደበኛነት የውሃ ፍሰቱም አይቋረጥም፤ ከሌሎች ሀገራት የተነጠለ አጠቃቀምም ይሁን በአግባቡ የውሃ ክፍፍል ባልተደረገበት ሁኔታ የሕዳሴ ግድቡ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት ይጎዳል ብሎ ማሰብ አይቻልም ነው ሉት መምህሩ፡፡

ግብፅ በ1929 (እ.ኤ.አ) ስምምነት መሠረት ወንዙን መጠቀም የሀገሪቱ ተፈጥሮኣዊ መብት እንደሆነ ታነሳለች፡፡ ይህ እሳቤ አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ በእነሱ ልክ የሚቀርብም ሆነ የሚሰላ ልማት የለም፤ ይህ ሳይኖር ለግብፅ ሀሳብ እውቅና መስጠት የኢትዮጵያን ወደ ፊት እዚህ ላይም ሆነ ሌሎች የግንባታ ሥራዎች (ፕሮጀክት) ላይ የመጠቀም ዕድል ያሳጣል፤ በዚህ ጉዳይ ድርድሮች በጥንቃቄ መመራት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት አቶ ዘውዱ፡፡ ከላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ውሃውን ለመስኖ የመጠቀም ዕድል ስላለ ወደፊት ሌሎች የግንባታ ሥራዎች (ፕሮጀክት) እየተፈጠሩ እንቅፋት እንዳይፈጥሩ በማሳብ ተፅዕኗቸውን ለመግታት የግብፅ ተወካዮች ምክክሩን በፍጥነት ለማድረግ እንደሚሹም አስረድተዋል፡፡

ያለ ዓባይ ህይወትም ሆነ ግብፅ የለችም የሚለው መከራከሪያ ነጥብ ምን ያህል ያስኬዳል ?

ግብፅ በርካታ አማራጮች አሏት ያሉት አቶ ዘውዱ ዋናው አማራጭ የከርሰ ምድር ውሃ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ የዓባይ ወንዝ የገፀ ምድር ውሃ ነው፤ በከርሰ ምድር ውሃ ግብፅ አቅሙ አላት፤ ጨዋማ ባህር ጨልፈው (ወስደው) ጥቅም ወደሚሰጥ ውሃ የመቀየር ሥራ ላይም ውጤታማ ናቸው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ የመስኖ እንቅስቃሴ ዝቅተኛ ነው፤ ከ80 በመቶ በላይ ማኅበረሰብ በድጋፍ ላይ የተመሠረተና ዝናብን በመጠበቅ የሚኖር ነው፤ ኢትዮጵያ አማራጭ አላት ቢሉም እነሱም አማራጭ አላቸው፡፡

በፊት የሕዳሴ ግድብ እንዳይገነባ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ አሁን ደግሞ መወያያ ነጥባቸውን የውሃ አሞላል ላይ አድርገዋል፡፡ የአስዋን ግድብ የውሃ መጠን እንዳይቀንስ ፍላጎታቸውን እያንፀባረቁም ነው፡፡

ሁለቱ ሀገራት ወደ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ?  

ቀጥተኛ ግጭቶች ይኖራሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከጦርነት ወጪ ስላለው ለእነሱ በእጃቸው ያለውን አማራጭ መጠቀም የተሻለ ስለመሆኑ መምህሩ አስገንዝበዋል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሀገራቱ ወደ ግጭት ሲጓዙ እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም፤ ነገር ግን በንጽጽር በዚህ ጊዜ በውስጣዊ የሀገር ጉዳይ ላይ ተንተርሰው በእጅ አዙር እንደ ጥሩ ዕድል ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብለዋል፡፡

አብመድ ያነጋገራቸው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ትዕዛዙ አያሌው ከሀገራቱ የተውጣጣ የጥናት ቡድን ቢኖርም መተማመን ሲፈጠር አላየንም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዋስትና የሚሰጥ መተማመኛ እንዲኖር የበለጠ ለመሥራት መሞከር እንዳለባትም ነው የተናገሩት፡፡ ያለስምምነት የሕዳሴ ግድብ ከተጠናቀቀ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላልም ብለዋል፡፡ ግብፅ ውስጣዊ ፖለቲካዊ ትኩሳቷ ከፍ ሲል የሕዝቡን ትኩረት ወደ ዓባይ የማዞር የተለመደ ዝንባሌ እንዳላት የጠቆሙት መምህሩ ጉዳዩን ለፖለቲካ ጉዳይ እየተጠቀሙበት ስለመሆኑ ግልጽ ነው ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ወንዙ በግድቡ ስፍራ እንደሚኖረው ዓመታዊ የፍሰት መጠን ከ4  እስከ 7 አመታትን በሚወስድ የሙሌት ደረጃ ግድቡን ለመሙላት፣ የግድቡን ሙሌት አጠናቅቆ ሥራ ከጀመረ በኋላም ድርቅ ከተከሰተ ውሃ ሳይንሳዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ሃሳቦችን አቅርባለች፡፡ ግብፅ ያቀረበችው ሃሳብ ኢትዮጵያ ግድቡን ከ12 እስከ  21 አመታት ውስጥ እንድትሞላ እንዲሁም ከመጀመሪያው ሙሌት በኋላ ኢትዮጵያ ለምትጠቀመው ውሃ ለግብጽ የተጠራቀመ የውሃ ጉድለት ማካካሻ እንድትሰጥ የሚያስገድድ ነው፡፡  ድርድሮች እና ውይይቶች ደግሞ ትርጉም ያለው ውጤት እና መሻሻል ሳያዩ አሁንም እንደቀጠሉ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በደቡብ አፍሪካ ጉብኝታቸው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፖሳ በሕዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ በአስታራቂነት እንዲሳተፉ መጠየቃቸው መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

ዘጋቢ፡-ኪሩቤል ተሾመ

 

Previous articleግብረ ገብነት ምን ላይ ነው?
Next article‹‹ቴዎድሮስ ገና ገና ወደፊት በሚመጣው የኢትዮጵያ ትውልድ ልብ ውስጥ እንደ እንቁ ያበራሉ፤ ቴዎድሮስ የአንድ ትውልድ ብቻ ንጉሠ ነገሥት አይደሉም፡፡›› ደራሲ አቤ ጉበኛ