“አንዳንድ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሆንግ ኮንግ ከባድ አውሎ ንፋስ መካከል ማረፍ መቻሉን የዘገቡበት መረጃ ትክክል አይደለም” አየር መንገዱ

79

ባሕር ዳር: ነሐሴ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ቁጥር ET608 የተመዘገበው አውሮፕላኑ በሆንግ ኮንግ ከባድ አውሎ ንፋስ መካከል ማረፍ መቻሉን ጠቅሰው አንዳንድ ሚዲያዎች የዘገቡበት መረጃ ትክክል አለመሆኑን አየር መንገዱ አስታውቋል፡፡ አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በባንኮክ ወደ ሆንግ ኮንግ ያደረገውን በረራ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ በበረራ ቁጥር ET608 የተመዘገበው አውሮፕላን መስከረም 1 ቀን 2023 በተያዘለት ሰአት በሆንግ ኮንግ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም ማረፍ መቻሉን ገልፆ፤ አንዳንድ ሚዲያዎች በረራው በሆንግ ኮንግ ከባድ አውሎ ንፋስ መካከል ማረፍ መቻሉን የዘገቡበት መረጃ ትክክል አለመሆኑን አስታውቋል።

አውሮፕላኑ ከባንኮክ ተነስቶ ወደ ሆንግ ኮንግ አየር ማረፊያ ሲደርስ ሊኖር የሚችለው የአየር ሁኔታ ደህንነቱ የተጠበቀ እንደነበር ከነበረው የአየር ትንበያ መረዳት መቻሉን አየር መንገዱ ገልጿል፡፡ በዚሁ መሰረትም የአየር ሁኔታው በተለመደው ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ እና ከሆንግ ኮንግ አየር ማረፊያ (ATC) ፍቃድ በመሰጠቱ በረራው እንዲቀጥል መደረጉን አስታውቋል።

የአየር መንገዱ የበረራ ቡድን አውሎ ንፋስ መከሰቱን ቀደም ብሎ ያውቅ እንደነበር የጠቀሰው አየር መንገዱ፤ የሚደረገውን በረራ ሙሉ እቅድ ከማውጣት ጀምሮ ለአብራሪ ሰራተኞች ፈጣንና መደበኛ መረጃ በመስጠት ይከታተል እንደነበርም ገልጿል፡፡ በረራው እንዲቀጥል የተደረገው አውሮፕላኑ ሆንግ ኮንግ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ከባድ አውሎ ንፋሱ እንደማይኖር የሚጠቁመውን የአየር ሁኔታ ትንበያ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደነበርም አየር መንገዱ አመልክቷል።

በዚሁ መረጃ መሰረት አንዳንድ ሚዲያዎች በረራው በሆንግ ኮንግ ከባድ አውሎ ንፋስ መካከል ማረፍ መቻሉን መዘገባቸው ትክክል አለመሆኑን የገለጸው አየር መንገዱ፤ አውሮፕላኑ በሆንግ ኮንግ አየር ማረፊያ ሲደርስ የነበረው የአየር ሁኔታ ማረፍ የሚያስችል እና ከቁጥጥር ውጭ ያልነበረ መሆኑን አስታውቋል፡፡

እንደ ኢቢሲ ዘገባ፤ በረራው በሰላም ከተጠናቀቀ በኋላ የሆንግ ኮንግ የአየር ሁኔታ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ አየር ማረፊያው ስራ ማቆሙን የጠቀሰው አየር መንገዱ፤ በዚህም ምክንያት የደርሶ መልስ በረራው ሰአት መራዙሙን ገልጿል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሚቀጥሉት 10 ቀናት በሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ በመጠንም ሆነ በሥርጭት እየቀነሰ ይሄዳል።
Next articleአዲስ አበባ የዓለም ቱሪዝም ከተሞች ፌደሬሽንን ተቀላቀለች።