ጋምቢ ህክምና እና ቢዝነስ ኮሌጅ ለ16ኛ ጊዜ በተለያዩ መርኃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ከ500 በላይ ተማሪዎች አስመረቀ።

68

ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጋምቢ ህክምና እና ቢዝነስ ኮሌጅ በተለያየ የሙያ መስክ ያሰለጠናቸውን 507 ተማሪዎች ያስመረቀ ሲሆን ከተመራቂዎች ውስጥ 288 ሴቶች ናቸው፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶክተር አዱኛ ጣሰው ለተመራቂዎች እና ተመራቂ ቤተሰቦች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ኮሌጁ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጥያቄ ምላሽ ለመሥጠት አሁን እያሰለጠነ ካለባቸው የትምህርት ዘርፎች በተጨማሪ ሌሎች የሙያ ዘርፎች ላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ጥያቄ ማቅረቡን አንስተዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች ዘርፈ ብዙ ችግር ባለበት ሀገር ሙያችሁን አክብራችሁ በመሥራት ለሀገራችሁ ችግር የመፍትሔ አካል እንድትኾኑ ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ለእውነት ቆማችሁ ማስመሰልን ተጸይፋችሁ ሙያችሁን አሳድጋችሁ ማኅበረሰቡን እንድታገለግሉ ሲሉም ለተመራቂዎች አደራ ሰጥተዋቸዋል፡፡

ዶክተር አዱኛ አያይዘውም በኮሌጁ ከሚማሩ ተማሪዎች ውስጥ 91 ነጥብ 9 በመቶ የሚኾኑት ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሠጠውን የመውጫ ፈተና ማለፋቸውን ተናግረዋል፡፡ ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ የጥናት እና ምርምር ሥራ እና ማኅበራዊ አገልግሎት በመሥጠትም ቀዳሚውን ሥፍራ እንደያዘ አንስተዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ እና ሪሰርች ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ገበየሁ፤ በርካታ ውጣ ውረዶች ቢያጋጥሟችሁም ችግሩን አልፋችሁ ለዚህ በመብቃታችሁ ደስ ይበላችሁ ብለዋል፡፡ ለሀገራችን ችግር መፍትሔ ትኾኑ ዘንድ ኀላፊነት አለባችሁም ብለዋል፡፡

ትምህርት የአንድ ጊዜ ኹነት ሳይኾን በየቀኑ በድግግሞሽ የምትማሩት ከዛሬው እናንተነት ወደ ነገው እናንተነት የሚያሳድጋችሁ የሕይወት ልምምድ ነው፡፡ ለነገው የሕይወት ፈተና ዛሬ ተመርቃችኋል፡፡ በቆይታ ጊዜያችሁ የቀሰማችሁን እውቀት በሥራ ዓለም ለሚገጥሟችሁ የእውነት ፈተናዎች መፍቻ ቁልፍ አድርጋችሁ ማኅበረሰባችንን እንድታገለግሉ ሲሉም አሳስበዋል ዶክተር መለሰ፡፡

ከተመራቂዎች መካካል የዋንጫ ተሸላሚዋ እና ሚድዋይፍሪ ያጠናችው ተማሪ ቤዛዊት በጤናው ዘርፍ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ቁርጠኛ መኾኗን ተናግራለች፡፡ማኅበረሰቡን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መኾኗንም አንስታለች፡፡ በአካውንቲንግ የተመረቀው አብርሃም ያለለትም በተማረው ትምህርት ማኅበረሰቡን በቁርጠኝነት ለማገልገል እና በዘርፉ የሚታየውን ብልሹ አሠራር በማስወገድ ሁሉንም በእኩል ለማገልገል መዘጋጀቱን ያነሳል፡፡

በህክምና ሳይንስ የተመረቀችው ዶክተር ይቤላ መላኩ በበኩሏ ሙያዋን አክብራ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ለመሥጠት ዝግጁ መኾኗን ተናግራለች። ጋምቢ ህክምና እና ቢዝነስ ኮሌጅ በጤና ሳይንስ እና ቢዝነስ ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ 408 ተማሪዎችን፣ በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ 10 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር 89 ተማሪዎችን በድምሩ 507 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል። ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ከ3 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁን ከኮሌጁ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረ ሲና ከተማ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በትብብርና በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ብርጋዴር ጀኔራል እሸቱ መንግሥቴ አሳሰቡ።
Next articleጎንደር ከተማ ወደ ሰላም መምጣቷን ተከትሎ ተጥሎ የነበረው የሰዓት ገደብ ወደ ምሽት 2:00 ሰዓት ተሻሻለ።