ግብረ ገብነት ምን ላይ ነው?

2273

 

ባሕር ዳር ጥር 5/2012ዓ.ም (አብመድ) በማንኛውም ኅብረተሰብ ውስጥ የእያንዳንዱ ሰው ድርጊት ወይም ጠባይ የሚገመገምበት ግብረገባዊ እሴት እንዳለ ይነገራል።

እነዚህ የግብረገብ እሴቶች በነባራዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት የተፈጠሩ እንጅ በሰዎች ነፃ ምርጫ የተገኙ እንዳልሆነም የተለያዩ ሰነዶች ያስረዳሉ።

የሰው ልጅ ውስጣዊ ማንነቱን የሚያንፀው እና ውጫዊ አካሉን የሚገነባው በምግብ እና በሳይንሳዊ ዕውቀቶች ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ግብረገባዊ እሴቶች ጭምር ነው።

ሁሌም ግብረ ገባዊ ግዴታ በሚገባ የሚከናወን ከሆነ ባሕሪም ሰናይ ምግባር የተላበሰ ይሆናል።

ግብረ ገባዊ እሴቶች በመማር እና በመላመድ የሚገኙ እንጂ በተፈጥሮ አብረው የሚወለዱ እንዳልሆኑም ይገለጻል፤ በእርግጥ የተፈጥሮ ፀባይም የራሱ አስተዋጽኦ አለው።

ግብረ ገባዊ እሴቶች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ያነጋገርናቸው ግለሰብ አሁንም ግብረገብ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ እና ቁጥራቸው ግን አናሳ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

የአማራ ብዙኃን መገናኘ ድርጅት የቀድሞ ባልደረባ ወይዘሮ መዓዛ ሳሙኤል እንደነገሩንና ዘግበንም እንደነበረው በአንድ ኤርትራዊ ቤት ተከራይተው ይኖሩ ነበር፡፡

ይሁን እንጅ የኢትዮ-ኤርትራ ግጭትን ተከትሎ ኤርትራውያን ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በላባቸው ያፈሩትን ቤታቸውን ትተው ነበር የወጡት፡፡

በወቅቱ በግለሰቦች ቤት ተከራይተው የነበሩት ወይዘሮ መዓዛ ኤርትራውያን ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በፍቅር እንደሸኗቸው አስታውሰዋል፡፡

አንድ ቀን በሁለቱ ሀገራት መካከል መልካም ግንኙነቱ እንደሚፈጠር ያስቡ እንደነበር የገለጹት ወይዘሮ መዓዛ የነበራቸው ተስፋ እውን ሆኖ ተከራይተው የቆዩበትን የቤት ኪራይ በባንክ ከማስቀመጥ ባለፈ ቤቱን በመጠገን እና በማደስ ጠብቀው ለባለ ንብረቶቹ አስረክበዋል፡፡

ይህን የታማኝነት ጥግ ከቤተሰቦቻቸው እና ከሚከተሉት ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ያገኙት ግብረ ገባዊ እሴት እንደሆነ ወይዘሮ መዓዛ ነግረውናል፡፡

ይሁን እንጅ በዚህ ወቅት መከባበር ታማኝነት፣ መረዳዳት፣ መቻቻል እና ሌሎችም መልካም እሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከሰሙ እንደሚገኙ ሐሳባቸውን አጋርተውናል፡፡

ለዚህ ደግሞ አሁን በሀገሪቱ የሚታየው ችግር ማሳያ መሆንኑ ያነሱት ወይዘሮ መዓዛ ወላጆች፣ መንግሥት እና የሃይማኖት ተቋማት የግብረ ግብ እሴቶችን የማስተማር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ትምህርት ክፍል የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ተጠሪ አባ በዓማን ግሩም እንደገለጹት ደግሞ የአንድ ሀገር ዜጋ ግብረ ገባዊ እንዲሆን መሠረቱ ቤተሰብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

አንድ ወላጅ ለልጁ የሚሰጠው ወይም የሚያሳየው ቤተሰባዊ መስመር እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ትልቅ መሠረት አንደሚጥል አባ በአማን ገልጸዋል፡፡

‹ልጅህን ስጠኝ እና እንደፈለከው አደርግልሃለሁ› የሚለው የሥነ ልቦና ሥነ ትምህርት ልሂቃን አባባል ወላጆች ለልጆች መልካም ግብረ ገብ ማበልጸጊያ መሠረቶች እንደሆኑ ማሳያ እንደሆነም ነው አባ በአማን የገለጹት፡፡

በመንፈሳዊ መጻሕፍቱ ላይም ‹ልጅህን ቅጣው፤ አድጎ እንዳያሳዝንህ› የሚለው መንፈሳዊ አባባል እንዳለ በመግለጽ ቅጣው ሲባል ግን መልካምነትን በማስተማር እንጅ ልጆችን በመደብደብ፣ በመቆጣት በማስፈራራት ግብረ ገብነትን እንዲላበሱ ማድረግ እንዳልሆነ ነው አባ በአማን ያስረዱት፡፡

ንጹሕ የሆነን ገንዘብ ብቻ ይዞ መቀጠል፣ የአደራ ዕቃን ማስቀመጥ አንዱ የኢትዮጵያውያን መልካም እሴት እንደነበር እና አሁንም እንዳለም አንስተዋል፡፡

እንደምሳሌ ያነሱት ደግሞ በባሕር ዳር እና በደብረ ማርቆስ የኤርትራውያን ቤትና ንብረት ለ20 ዓመታት ያህል ጠብቀው ያስረከቡ ግለሰቦችን ነው፡፡

በኢትዮጵያ እየታዬ ያሉት የግብረ ገብ እሴቶች ከውጩ ግብረ ገባዊ እሴቶች ጋር በማነጻጸር ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙም አባ በአማን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በሀገራችን ላይ የሚታውን የግብረ ገብ እሴት ከውጩ ሀገራት ግብረ ገብነት ጋር ማነጻጸር ከጀመርን የግብረ ገብ እሴታችንም ከድኅህነታችን ጋር ወርዶ ከደረጃ በታች ነው፡፡ ግብረ ገብን በሀገራት ደረጃ ማነጸጸር ከጀመርን ዝቅተኛ ደረጃ ስንሆን ከጊዜ አንፃር ካነጻጸርነው ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የግብረገ ብ ግድፈቶች እየጨመሩ ነው›› ብለዋል አባ በአማን፡፡

ከዓለም አቀፋዊነት ጋር ተያይዞ የሚለቀቁ ነገሮች፣ ከሰብዓዊነት ይልቅ ለገንዘብ ትኩረት መስጠት ለግብረ ገብ መሸርሸር በምክንያትነት ተቀምጠዋል፡፡

ቤተሰብ፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት እና ቤተ እምነቶች ደግሞ ግብረ ገባዊ እሴቶችን እና ሕግጋትን በመፍጠር ወይም በመቅረጽ፣ በማክበር እና በማስከበር፣ በማወቅና በማሳወቅ፣ በመረከብ እና በማስተላለፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ማኅበራዊ ተቋሞች ቢሆኑም በመንግሥት በኩል ለግብረ ገብ ትኩረት አለመሰጠቱን ነው መምህር አባ በዓማን የገለጹት፡፡

መንግሥትም በሀገሪቱ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች የሚጠቀሙባቸውን የጋራ የሆኑ መልካም እሴቶችን በሥርዓተ ትምህርት በማካተት መስጠት እንደሚገባው አባ በዓማን አሳስበዋል፡፡

ሥርዓተ ትምህርቱም ሲቀረጽ ሊቃውንቱ በትኩረት መርምረው አካታች በሆነ መንገድ መውጣት እንዳለበት አባ በዓማን ተናግረዋል፡፡

ቤተ እምነቶችም ዜጎችን በሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር የማነጽ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው›› የሚለው ሥነ መለኮታዊ ወርቃማ ሕግ እንዳለም አንስተዋል፡፡ ይህንንም አስተምሮ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት አጠናክረው ሊቀጥሉበት አንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

Previous articleበኩር ጋዜጣ ጥር 04-2012 ዓ/ም ዕትም
Next articleድርድሮች በጥንቃቄ መመራት እንዳለባቸው ምሁራን አሳሰቡ፡፡