
ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በደብረ ሲና ከተማ አኹን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በትብብርና በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ የቀጣናው ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ብርጋዴር ጀኔራል እሸቱ መንግሥቴ አሳስበዋል።
ብርጋዴር ጀኔራሉ ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት በወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ከደብረ ሲና ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕገ-መንግሥቱንና ሕግን የማስከበር የሀገር ውስጥና የውጭ ጠላት መከላከል ተቀዳሚ ተልዕኮ መሆኑን አንስተዋል።
በአንድ ሀገር ሁለት የታጠቀ ኃይል ሊኖር እንደማይችልና በጦርነት ስልጣን መያዝ እንደማይቻል ያነሱት ጀኔራሉ ክልሉ ሰላም ከሆነና ችግሩ ከቆመ ሠራዊቱ ወደ ካምቡ እንደሚመለስም ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የዞን አስተባባሪ አቶ ዓይነኩሉ አበበ በየደረጃው የሚመደበው አመራርና የመንግሥት ሠራተኛው ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ችግሩ መፈጠሩን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ችግሩ በጦርነት ሳይሆን በውይይት መፍታት ሲገባ ጦርነት ውስጥ መግባት ተገቢ አይደለም በዚህም ግጭቱ በክልሉ አቅም ሊፈታ ባለመቻሉ የፌዲራል መንግሥቱ ጣልቃ መግባቱን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣሉን ጠቁመው ኅብረተሰቡ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም ማስከበር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሰሜኑ በነበረው ጦርነት ከተከሰተው ችግር ሳናገግም ሌላ ጉዳት ውስጥ መግባታችን አሳዝኖናል ብለዋል።
በውይይቱም በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጠረው ሁሉን አቀፍ ችግር መፍትሔ ማምጣት የሚቻለዉ ሁሉም በቀናነት ለመፍትሔው ሲተባበር እንደሆነም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!