
ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከክልሉ የጸጥታ ምክር ቤት አባላት ጋር ምክክር እያካሄዱ ነው።
የክልሉ የጸጥታ አደረጃጀት በክልል ደረጃ አዲስ መዋቅር መሥራቱን ተከትሎ አደረጃጀቱ በፍጥነት እስከ ታችኛው አካል ድረስ ይወርዳል ተብሏል።
በክልል ደረጃ የተካሄደው የጸጥታ አደረጃጀት የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል። አደረጃጀቱን እሰከ ከታችኛው መዋቅር ድረስ በፍጥነት ማውረድ ያስፈልጋል ተብሏል።
ከአደረጃጀቱ ጎን ለጎን የክልሉን ሰላም በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ እየተሠራ እንደሆንም ተነስቷል። የክልሉ የጸጥታ መዋቅር የሕዝብን ጸጥታ የሚያውኩ ችግሮችን በመለየት በፍጥነት መሥራት እንዳለበትም ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አንስተዋል።
ፈጥኖ ወደ ሥራ መግባት እና አሁን ያለውን የጸጥታ ሥራ ማገዝ በሂደትም ተክቶ መሥራት የቀጣይ ጊዜ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑ አጽንኦት ተሰጥቶት በውይይቱ ተነስቷል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!