
ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከብራዚል ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት በአዳዲስ የትብብር መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥር በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ዣንዲር ፌሔይራ ዶስ ሳንቶስ ተናገሩ።
አምባሳደሩ ለኢዜአ እንደገለጹት ብራዚልና ኢትዮጵያ በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።
በተለይም ሁለቱ ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመው ለዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው የገለጹት።
ሁለቱ ሀገራት በግብርና ዘርፍ ላይ ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው ጠቁመው በስፖርት ዘርፍም ልምድ መለዋወጥ የሚያስችል አጋርነት መመስረታቸውን ተናግረዋል።
ይህ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይም የተጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከብራዚል ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት በአዳዲስ የትብብር መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥር አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
ብሪክስ አዲስ የልማት ባንክ፣ የብሪክስ ቢዝነስ ምክር ቤትና የብሪክስ የሴቶች የቢዝነስ አጋርነት የመሰሉ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በውስጡ የያዘ መሆኑን አንስተው ይህም የግንኙነት አድማሱን ይበልጥ ለማስፋትና ለማጠናከር ዕድል እንደሚሰጥ ነው የገለጹት።
ይህም ሁለቱ ሀገራት በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በስፖርትና በሌሎችም መስኮች ግንኙነቱን ለማጠናከር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በዓለም አቀፍ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ድምጽ እንዲሰማ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ፍሬያማ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት።
በተለይም ዓለም አቀፍ ሕግን ያከበረ ሁሉን አቀፍ የባለ ብዙ ወገን ግንኙነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማጠናከር የሚደረገውን አዎንታዊ ጫና ያጠናክራል ብለዋል።
በተጓዳኝም የባለብዙ ወገን የፖለቲካና የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርም እንዲያደርጉ የሚደረገውን ግፊት ወደ ፊት በመግፋት አበርክቶው ትልቅ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በተለይም በደቡብ ለደቡብ የትብብር ማዕቀፍ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ለማስተሳሰር የሚደረገው ጥረትንም እንደሚያጠናክረው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያና የብራዚል የሁለትዮሽ ግንኙነት ከተጀመረ 70 ዓመታትን አስቆጥሯል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!