
ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ50 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል ከነሐሴ 23/2015 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው፡፡ በክልሉ የሕግ ማስከበር ሥራ የነበረባቸው አካባቢዎች ወደ ሰላም ተመልሰው ተማሪዎችን እየመዘገቡ ነው፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ተክለዮሐንስ ኃይለጊዮርጊስ ደብረ ብርሃን ከነበረችበት የሰላም እጦት ወጥታ መደበኛ ሥራዋን እያከናዎነች መሆኗን ገልጸዋል፡፡ በከተማ አሥተዳደሩ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ከመሪዎች፣ ከወላጆች፣ ከመምህራን፣ ከርእሰ መምህራን፣ ከሱፐር ቫይዘሮች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ ወደ ሥራ ምግባታቸውን ነው ምክትል ኅላፊው የገለጹት።
ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም በከተማ አሥተዳደሩ በአምስት ክፍለ ከተሞች በተመረጡ አምስት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በንቅናቄ ማስመዘገባቸውንም ተናግረዋል፡፡ በአንድ ቀን በተደረገው ምዝገባ በየትምህርት ቤቶቹ ከ72 እስከ 84 በመቶ ተማሪዎችን መመዝገብ መቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ 81 ትምህርት ቤቶች እስከ ነሐሴ 26/ 2015 ዓ.ም በከተማው ይመዘገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ መደበኛ ተማሪዎች 69 በመቶ የሚሆኑት ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር አቅራቢያ በሚገኙ የገጠር ወረዳዎች የሚኖሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጊዜው ገና ነው በሚል እና በሌሎች ምክንያቶች መዘግየት እንዳለም ተናግረዋል፡፡
ከመደበኛ ተማሪዎች ባለፈ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን እየመዘገቡ መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል መምሪያ ኃላፊው 62 በመቶ የሚሆኑ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን መመዝገባቸውን ነው የገለጹት፡፡
የጎልማሳ ትምህርት ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በጎልማሳ ትምህርት ይመዘገባሉ ተብሎ ከሚጠበቁት መካከል 24 በመቶ መመዝገባቸውም ገልጸዋል፡፡
በልዩ ፍላጎት ትምህርት ይመዘገባሉ ተብሎ ከሚጠበቁት መካከል 18 በመቶ የሚሆኑት መመዝገባቸውንም ተናግረዋል፡፡ በልዩ ፍላጎት እና በጎልማሳ ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በተሠራው ሥራ ላይ ውይይት እና ግምገማ ተካሂዶበት ተማሪዎችን በንቅናቄ የማስመዝገቡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡
ከተማዋ ሰላማዊ መሆኗን ያነሱት ምክትል መምሪያ ኃላፊው ወላጆች ልጆቻቸውን እየላኩ እንዲያስመዘግቡም አሳስበዋል፡፡ የመማር ማስተማር ሂደቱ መቋረጥ እንደሌለበት ሊታወቅ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ከምዝገባው ጎን ለጎን የመጽሐፍ ሥርጭት እተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የሀገር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በለማ ትውልድ ስትመራና ሀገር ወዳድ ዜጋ መፍጠር ሲቻል መሆኑን ያነሱት ምክትል መምሪያ ኃላፊው ትውልዱን ዛሬ ማነጽ የቀጣዩን የሀገር እጣ ፋንታ መወሰን ነው ብለዋል፡፡ ትውልድን ለማነጽ የሁሉም ድርሻ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ይህን ለማሳካትም ተማሪዎችን በንቅናቄ ማስመዝገብ ግድ እንደሚልም አመላክተዋል፡፡
ወላጆች ልጆቻቸውን በወቅቱ ማስመዝገብ ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡ የትምህርት ተቋማትም ለመማር ማስተማሩ ምቹ መሆን አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ለትምህርት ሥርዓቱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በከተማዋ ይመዘገባሉ ተብሎ ከሚጠበቁት 50 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከ34 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ተመዝግበዋል ተብሏል፡፡
በቀጣይ ሳምንት ምዝገባውን በተሟላ መንገድ ለማጠናቀቅ እየሠሩ መሆናቸውን የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አስታውቀዋል ፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!