“ለሀገር የቆመ፣ ለሠንደቅ የቀደመ-ሕዝብ”

48

ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገሩን ከነብሱ ያስቀድማል፣ ስለ ሀገር ይመነምናል፣ ስለ ሀገር ምቾትና ተድላን ይጥላል፣ ደም በፈለገች ጊዜ ደሙን ያፈስሳል፣ ሀገሩ አጥንት በፈለገች ጊዜ አጥንት ይከሰክሳል፣ ጥበብ በፈለገች ጊዜ ምድሯን በጥበብ ያረሰርሳል።

ለሠንደቋ እጅ ይነሳል፣ ሠንደቋን የሚነካትንም እጅ ያስነሳል፡፡

ለዘመናት ተዋድቆላታል፣ ሞቶላታል፣ ደምቶላታል፣ በደምና በአጥንቱ፣ በላቡ ጸንቶ አጽንቷታል፡፡ ጠላቶች ቢበረክቱባትም፣ መከራ ቢጸናባትም፣ የዘመን ተራራው ቢበዛም፣ እሾህና አሜካላው ቢያይልም፣ ጦር የሚሰብቁት ባያቋርጡም ሀገሩን እና ሠንደቁን አይተውም፣ ሠንደቁን አስቀድሞ ሀገሩን ይጠብቃታል፣ ጠላቶቿን ሁሉ ቀጥቶ አደብ ያስገዛላታል፡፡

ጠቢብ ነው አብያተ ክርስቲያናትን በዓለት ላይ ያንጻል፣ በዓለት ላይ ይጠበባል፣ ዓለትን እንደ ግራምጣ ይሰነጥቃል፣ እንደ አሽከር ያዝዛል፤ የድንጋይ መልክ ያወጣል፣ የተዋቡ አብያተ መንግሥታትን ጡብ ደርድሮ ይገነባል፣ ባመሩ አብያተ መንግሥታት፣ ብልሃትን የተቸሩ፣ አምላካቸውን የሚፈሩ፣ ሕዝባቸውን የሚያከብሩ፣ በሕግና በስርዓት የሚኖሩ፣ በፍቅር የሚመሩ መንግሥታትን ያነግሳል፡፡

በሐይቅ ላይ ደብር ይደብራል፣ ገዳም ይገድማል፡፡ ፊደላትን ይቀርጻል፣ ቀለም በጥብጦ፣ ብራና ፍቆ ታሪክ ያሰፍራል፣ በወርቅ ቀለም አስቀምጦ ለትውልድ ሁሉ ያቆያል፡፡ ምስጢራትን ያመሴጥራል፣ እውቀትን ሁሉ ይነግራል፣ ያስተምራል፡፡
ሃይማኖተኛ ነው በማለዳ የአዛን ድምጽ ሰምቶ ለሶላት ይነሳል፣ ሶላቱን አሰላምቶ ለሀገሩ ሰላምና ፍቅርን፣ ደስታና በረከትን ከአምላኩ ዘንድ ይለምናል፡፡

ካህኑ የቤተክርስቲያን ደወል ሲደውሉ፣ ነጭ እየለበሰ ለኪዳን ይገሰግሳል፣ ማረን፣ ይቅርም በለን እያለ በተመስጦና በደግነት ቅዳሴ ያስቀድሳል፣ ይጾማል፣ ይጸልያል፣ አምላክ ሀገሩን እንዲጠብቅለት፣ የሀገሩን ጠላቶች ፈጥኖ እንዲያስገዛላት፣ መከራዎችን እንዲያርቅላት፣ ድርቅና፣ ረሃብ፣ በሽታና ክፉ ቀን እንዳይገጥማት፣ ፍቅርና ተድላን እንዲያድላት፣ መልካሙን ዝናብ እንዲያዘንብላት፣ ምድሯንም በአዝመራ እንዲባርካት፣ ደስታና ተድላ እንዳይለያት፣ ሕገ እግዚአብሔር እንዳይጠፋባት፣ ሕግና ስርዓት ጸንቶ እንዲኖርባት፣ መሀሏን ገነት እንዲያደርጋት፣ ዳሯን ሳት አድርጎ እንዲጠብቃት አብዝቶ ይማጸናል፡፡

ደግ ነው በደግነት ይኖራል፣ ፈትፍቶ ያጎርሳል፣ የራሱን አውልቆ ለሌላው ያለብሳል፣ ትሁት ነው የታላቆቹን ጉልበት ሊስም ይጎነበሳል፣ በትህትና እጅ ይነሳል፡፡ እጅ የሚነሳው፣ ጉልበት ለመሳም የሚጎነበሰው በፍቅርና በአክበሮት ሲሆን እንጂ በሌላ አይደለም፡፡

ብልህ ነው ሕግና ስርዓትን ይሠራል፣ ሕግ አክባሪ ነው ሕግና ስርዓትን ያከብራል፣ የሰማይና የምድሩን ሕግጋት አብዝቶ ይጠብቃል፣ ጠብቆም ያስጠብቃል፡፡ አበውና እመው የሚሉትን በትህትና፣ በቀና ልቡና ይሰማል፡፡ የሰማውንም ይተገብራል አማራ፡፡

ሠንደቋን አብዝቶ ከማክበሩ የተነሳ በሠንደቁ አምላክ ከተባለ ለጥል አይነሳም፣ ሠንደቋ ከተነሳች የሰነዘረውን ጎራዴ ወደሰገባው ይመልሳል፣ ያዞረውን አፈሙዝ ያዞራል፤ ለሠንደቋ ሲል ሁሉን ይተዋል፡፡ በእርሷ ከማለም አይመለስም፡፡ ሠንደቋን አብዝቶ ያከብራታል፣ ከዘመን እስከ ዘመን ሳያቋርጥም ይጠብቃታል፡፡

በዓት ዘግተው፣ ወገባቸውን በገመድ አስረው፣ እፍኝ ቆሎ በልተው ለሀገራቸው እና ለዓለሙ ጸሎት የሚያደርሱ ጻድቃን አበውና እመው የሚገኙበት፣ ጀንበር ሳትዘልቅ ጠምዶ፣ ጀንበር እስክትጠልቅ ድረስ በሮችን ጠምዶ የሚያርስ፣ በሰፊ አውድማ ላይ ነጭና ጥቁር የሚያፍስ፣ ለተራበ ሁሉ የሚደርስ ኩሩ ገበሬ የሚኖርበት፣ ሀገር ተነካች ሲባል ቀንበሩን ሰቅሎ፣ ልጆቹን ጥሎ፣ ማሳውን ጾም አሳድሮ የራሱን ስንቅና ትጥቅ ይዞ የሚዘምት ጀግናና ኩሩ ያለበት፣ ለምድሩም ለሰማዩም የተመቸ ነው አማራ፡፡

አማራ የሀገር ክብርንም ከፍ ያደርጋል፡፡ ለተከበረች ሀገሩ፣ ምልክቱና መለያው ለሆነች ሠንደቁ ሲል ይራባል፣ ይጠማል፣ በእሾህና በአሜካላ መካከል ይረማመዳል፣ በጦርና በሰይፍ ፊት ይጓዛል፣ ሞትን እየናቀ ወደ ፊት ይገሰግሳል፡፡

በሪሁን ከበደ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው የአማራ ሀገር ወዳድነት ኃያል እንደሆ፣ ሀገር ተነካች ሲባል ሁሉን ረስቶ ሀገር ወደ ምትድንበት አቅጣጫ መዝመቱ ከጥንት ጀምሮ የነበረ እና ያለ እንደሆነ ጽፈዋል፡፡ ሀገር ተነካች ሲባል እንኳን መኳንንቱ፣ እንኳን መሳፍንቱ፣ እንኳን የጦር አበጋዞች፣ እንኳን ጦር ጋር ኖረው ጦር ጋር የሚከርሙት የጦር አዋቂዎች፣ በሬዎች ጠምዶ ነጭና ጥቁር የሚያፍሰው፣ ወተትና ማር የሚያፈስሰው ገበሬው ሞፈር ቀንበሩን ሰቅሎ፣ ስንቅና ትጥቁን ጠቅልሎ፣ ልጆቹን በባዶ ቤት ጥሎ ሀገር ተነካች ወደ ተባለችበት ንፍቅ ሁሉ በቁጣ ይገሰግሳል፡፡

ከነገሥታቱ ጋር ሆኖ የሀገሪቱን ዳር ድንበር ጠብቆ ነጻነቷን አስከብሮ ለአሁኑ ትውልድ ያቆየው የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኩሩና ጀግና ኢትዮጵያን ጋር መሆኑንም በሪሁን ከበደ ጽፈዋል፡፡ ከጠላት ተከላክሎ ነጻነቷን ጠብቆ ባያቆያት ኖሮ ለአሁኑ ትውልድ ይች ሀገር በቀኝ ግዛት ሥር ሆና ነበር የምትቆየውም ብለዋል፡፡

“ያለ ሀገር ነጻነት፣ ያለ ሕዝብ አለቅነት” አይገኝም እንዲሉ አበው ጀግኖች ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ነብሳቸውን ገብረው ጠብቀዋት ባይቆዩ ነጻነቱም፣ ሹመቱም አይገኝም ነበር ብለዋል በሪሁን ከበደ በመጽሐፋቸው፡፡ አበው ልበ ኩሪዎች እና ጀግኖች ናቸውና ነጭ ልብስ ለብሰው፣ ጎራዴ ሥለው፣ ጦር አሹለው፣ ጋሻ አስተካክለው ነው ሀገር ያቆዩት፡፡ የድፍረታቸውን እና የጀግንታቸውን ልክ ሲያሳዩ ከጠላት ዓይን የሚያርቃቸው ከቅጠሉ፣ ከአፈርና ከድንጋዩ ጋር የሚያመሳስላቸው ልብስ እንኳን መልበስ አልፈለጉም፡፡ ነጭ ለብሰው፣ በግጥ እየታዩ፣ ጠላትን መጣንልህ እያሉ ታግለው ድል ያደርጋሉ እንጂ፡፡

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ በሚለው መጽሐፋቸው አማራዎች ጠበው መኖር አይፈልጉም፣ አይወዱም፣ መላዋ ኢትዮጵያ የእኛ ናት ብለው ነው የሚያስቡት ብለዋል፡፡ አማራዎች በሁሉም አቅጣጫ የተነሱ የኢትዮጵያ ጠላቶችን እየዘመቱ ከሌሎች ኢትዮጵያውን ጋር ድል እንደመቱ ሁሉ መላዋ ኢትዮጵያም በሰላም የሚኖሩባት፣ የእነርሱ እንደሆነች ያምናሉ፣ በዚህ እምነታቸውም በመላዋ ኢትዮጵያ ለዘመናት ኖረዋል፤ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም በመላዋ ኢትዮጵያ እንደ አሻቸው መኖር አለባቸው ብለው ያምናሉ፤ በዚህ እምነታቸውም ይጸናሉ፡፡

አማራ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የጸና ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ አይጎድልም፣ የኢትዮጵያዊነት ውስጣዊ እና እውነተኛ መንፈሱም ለዘመናት አይቀንስም፡፡ አማራ ከሌሎች ወንድምና እህቶቹ፣ አብዝቶ ከሚወዳቸውና ከሚመካባቸው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ሲጠብቅ ኖሯል፡፡ አሁንም እየጠበቀ ነው፡፡ ወደፊትም ይጠብቃል፡፡

የቅርቡን ስናስታውስም ኢትዮጵያ በተፈተነችበት እና በተወጋችበት የህወሃት ወረራ ለሠራዊቱ ደጀን በመሆን የአማራ ሕዝብ አስተዋጽዖ ላቅ ያለ ነበር፡፡ ሠራዊቱ ሲካድ ቀድሞ ደርሷል፡፡ በግፍ የተወጋውን ሠራዊት ደም አብሷል፡፡ የማይናወጽና እስከ ሞት ድረስ የሚታመን ደጀን መሆኑን አሳይቷል፡፡ ሀገር ለማጽናት በተደረገው ጦርነት ሠራዊቱን አልብሷል፣ ምሽግ ድረስ እየሄደ፣ በሚተላለፍበት በመንገዱ እየጠበቀ በመሶብ እንጀራ እየያዘ አጉርሷል፣ ሲጠማው ወተትና ማር አጠጥቷል፣ ሲቆስል አክሟል፣ ሲሰዋ በክብር በተከበረ ሥፍራ አሳርፏል፡፡ ከዚህ አልፎ አብሮ ተሰልፎ እልፍ መስዋእት ከፍሏል፡፡ አሰፍስፈው የመጡትን ጠላቶቹን ድል መትቷል፡፡

ሀገር ለማጽናት በተደረገው ተጋድሎ በጅምላ ተገድሏል፣ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘቡን አጥቷል፡፡ ሀገር ያለ መስዋእትነት አትጸናም በሚለው የጸና መርሁ ለሀገር አያሌ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ ለሀገር የቆመ፣ ለሠንደቅ የቀደመ ነውና፡፡

አማራ በየዘመናቱ የገጠሙትን ችግሮች በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በብልሃት፣ በአንድነት እና በሰላም ሲፈታ ኖሯል፡፡ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ታላቅ ክብር ይሰጣል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትንም ከሁሉ ያስቀድማል፡፡ ዛሬም ለገጠሙት ችግሮች ሁሉ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን እያስቀደመ መፍትሔ ያበጃል፡፡ የበዙ ችግሮች ገጥመውት በጥበቡ ፈትቷቸዋል፡፡ በአበው ምክር እና በቆየው ወግና ስርዓት ተሻግሯቸዋል፡፡ ዛሬም የገጠሙትን ችግሮች በጥበቡ፣ በቆየው ብልሃቱና እሴቱ ይሻገራቸዋል፤ ያልፋቸዋል፡፡

ችግሮቹን ፈትቶ፣ ፈተናዎቹን ተሻግሮ ወዳጆቹን ያኮራቸዋል፤ ጠላቶቹን አንገት ያስደፋቸዋል፡፡ ይሄን ማድረግ ደግሞ ያውቅበታል፡፡ አማራ በብልሃት፣ በፍቅርና በሰላም ጥቅሙን እና ክብሩንም ያስከብራል፡፡ ፍትሕን ለራሱ፣ ፍትሕ ለሚሹ ሁሉ ይሆን ዘንድ ይሠራል፡፡

ትናንት ኢትዮጵያን ሲል ኖሯል፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ ይላል፡፡ ወደፊትም ኢትዮጵያ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ትክ የሌላት፣ ክብሩንና ማዕረጉን የሚገልጥባት ሀገሩ ናትና፡፡ አማራ ለሀገር እንደቆመ፣ ለሠንደቅ እንደቆመ ይኖራል፡፡

ለፍትሕ፣ ለአንድነት፣ ለእኩልነት እና ለጸና ኢትዮጵያዊነት መኖር መገለጫውና ባሕሪው ነው፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለ70 ሺህ 400 ሥራ አጥ ወጣቶች የገጠር መሬት እንደሚያቀርብ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ገለጸ።
Next article“ትውልዱን ዛሬ ማነጽ የቀጣዩን የሀገር እጣ ፋንታ መወሰን ነው ” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ