
ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአብሮነት ውስጥ የሚፈጠር ግጭት ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በብሂላቸው “እግር እና እግር እንኳን ይጋጫል” ይላሉ፡፡ ሕዝብ እና መንግሥት፣ መሪ እና ተመሪ፣ ታላቅ እና ታናሽ፣ ወዳጅ እና ጎረቤት በሚኖራቸው መስተጋብር ልክ የሚጋጩበት አጋጣሚም ሰፊ ነው፡፡
ከግጭት የሚገኝ ኪሳራ እንጂ ትርፍ ባይኖርም ኪሳራውን የከፋ የሚያደርጉት ሌሎች ውጫዊ ተፅዕኖዎች ደግሞ ይኖራሉ፡፡ እጅ የበዛበት ግጭት መቋጫው ሩቅ ፤ የልብ ስብራቱ ጠሊቅ ነው፡፡
በግጭት መነገድ ከሰብዓዊነት የወጣ እንስሳዊ ተግባር ነው፡፡ ግጭትን ማብረድ፣ ሰላምን ማውረድ እና ልዩነትን ማጥበብ የሚያስችሉ ሃገር በቀል የሽምግልና እና የግልግል ሥርዓት በኢትዮጵያ አያሌ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡
“አንተም ተው አንተም ተው” ብለው ጥላቻን የሚያበርዱት ሽማግሌዎች የፍትህ አደባባያቸው የዛፍ ጥላ፤ መቀመጫቸው ሰቀላ ነበር፡፡ እነዚህ የሀገር ሽማግሌዎች በማሕበረሰቡ ዘንድ ከፍ ብለው የመቀመጣቸው ምስጢርም ላቅ ያለው ስብዕናቸው ሀገረ-መንግሥታዊ ቅቡልነት የተቸረው መሆኑን ተከትሎ ነው፡፡
ተናግረው የሚደመጡ፣ አጥፊን የሚቀጡ፣ አልሰማም ያለን የሚቆጡ እና ህጻናትን የሚቆነጥጡ ሽማግሌዎች ፈጽሞ ባልጠፉባት ሀገር ለምን መደማመጥ ተሳነን ብሎ መጠየቁ ወቅታዊ እና ተገቢ ነው፡፡
ግጭት ተፈጥሯዊ ክስተት ነው በሚለው ሃሳብ የሚስማማ ኹሉ ከግጭት ለመውጣት በሚያስችሉ የመፍትሄ አማራጮች ዙሪያ መግባባት ላይ መድረስም ግድ ይለዋል፡፡ ከግጭት ለመውጣት ብቻ ሳይሆን በግጭት ውስጥ ተስፋ ሳይቆርጡ ለመቆየትም መደማመጥ አስፈላጊ ነው፡፡
በዘመናዊት ኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ምስረታ ስምረት ውስጥ የሰከነ የመረጃ ቅብብሎሽ ሥርዓት አይተኬ ሚና ነበረው፡፡ ዳጉን የመሰለ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ያነበረ ማሕበረሰብ እና “ነገርን አዳምጦ እህልን አላምጦ፤ ነገርን ከስሩ ውኃን ከጥሩ” እየተባለ መደማመጥ እና መስከን እንደ አንድ አይነኬ እሴት የሚሰበክባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ነገር ግን ድህረ ዘመናዊነትን ተከትሎ የመጣው የበይነ-መረብ ክስተት የሥነ-ተግባቦት እና ጋዜጠኝነት አውዱን ምቹ የግጭት መፈልፈያ ማጀት እንዳደረገው እያየን ነው፡፡
የቴክኖሎጂ ኑፋቄ እና የኒዩክሌር ጦርነት የሚያምሷት ዓለም የመረጃ አምልኮም አዲስ ክስተት ሆኖ ብቅ ብሎባታል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ በርካቶቹ ሀገራት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ መሰል የመረጃ ወከባ ውስጥ ሲገቡ አስተውለናል፡፡
በፊሊፒንስ የተከሰተው እና የቀለም አብዮትን የወለደው ግጭት ምንም እንኳን ፕሬዚዳንት ፈርዲናንድ ማርቆስን ከመንበራቸው ቢያወርድም ለፊሊፒንሳዊያን የተረፈው ጦስና ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ መናጋቶች ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ እንኳን ሙሉ በሙሉ መጠገን አልተቻለም፡፡ ፊሊፒንስ እንደ ምዕራባዊያኑ የዘመን ቀመር 1898 ከአሜሪካ ሞግዚትነት እንደተላቀቀች ቢነገርም ለበርካታ ዘመናት ዕውቅና ተነፍጓት ቆይታለች፡፡
ፊሊፒንስ በ1935 እ.አ.አ የራሷን መንግሥት መሥርታ ሉዓላዊ ሀገረ-መንግሥት ብትመሰረትም እንደ ሀገር ዕውቅና ያገኘችው ግን 1946 እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ለዘመናት የተጣባት የውጭ ኃይሎች ያልተገባ ጣልቃገብነት ያጎሳቆላት ፊሊፒንስ “ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በ1986 የተከሰተው የቀለም አቢዮት ጦስ ከ35 ዓመታት በኋላ እንኳን ከፍላ ያልጨረሰችው መቀመቅ ውሰጥ ከትቷት አልፏል ይባላል፡፡
የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት እና “ቦንቦንግ” በሚል ቅጽል መጠሪያ የሚታወቁት ፈርዲናንድ ሮዋልዴዝ ማርቆስ ጁኒየር ራሳቸውን እና ሹማምንቶቻቸውን እዳ ከፋይ አድርገው ይቆጥራሉ ይባላል፡፡ “በታሪክ አጋጣሚ እንደ መጣ አንድ ፕሬዚዳንት ፊሊፒንሳዊያንን እና ፊሊፒንስን የመምራት ዕድል ትከሻየ ላይ ሲወድቅ ካለፈው ተምረን ለእያንዳንዱ ዜጋ ሰላምን ለማስፈን እሰራለሁ፡፡ ሀገሪቱን ከተጣባት የግጭት ደዌ ለመፈወስ እና ለግጭት ምክንያት የሆነውን ድህነትን ለማከም ደግሞ እኔ ብቻ ሳልሆን እያንዳንዱ ፍሊፒንሳዊ እዳ ከፋይ ሆኖ ሊሰራ ግድ ይላል” ይላሉ፡፡
ትናንት የፖለቲካ ሥርዓት ስብራት የወለደው ቅራኔ እና ቁርሾ ይኖራል፡፡ ቅራኔ እና ቆርሾ በጊዜው ሳይታከም እየዋለ ሲያድር ያመረቅዛል፡፡ ጋንግሪን የመጨረሻው የህመሙ ክፍል የሚሆንበት አጋጣሚም እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ጋንግሪን ከተከሰተ በኋላ የመጨረሻ ፈውሱ መቆረጥ ነው፤ ላለመቆራረጥ እድሉ እስካለ ድረስ የሰላም አማራጮችን መጠቀም ግን ብልህነት ነው፡፡ “ሽማግሌ እና ሽምግልና ፈጽሞ ባልጠፋባት ኢትዮጵያ የግጭት ነጋሪት ለምን አብዝቶ ይጎሰማል” ብሎ ማሰብ ፍቱን መፍትሄ ነው፡፡
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!