“ስንወያይ፣ ስንመካከር እና ስንደማመጥ ችግሮቻችን ሁሉ ከኛ በታች ይሆናሉ” ዶ.ር መንገሻ ፈንታው

89

ባሕር ዳር: ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶ.ር መንገሻ ፈንታው ከሰራተኞች ጋር ትውውቅ አድርገዋል። በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በክልላችን የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ የተመደበው አዲስ አመራር ሕዝባችን ያጋጠመውን ፈተና በድል መወጣት እንዲችል መላው ሕዝብ ድጋፍ ሊያደርግለትና ፈጥነን ወደ ጋራ ልማትና ብልጽግና ልንገባ ይገባል ብለዋል።

ሀገራዊና ክልላዊ መግባባት በመፍጠር ሕዝባችን የገጠመውን ፈተና በድል ለመወጣት መላው ሕዝባችን ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። በክልላችን የገጠመውን ችግር በአጭር ጊዜ በመፍታት ወደተሟላ ሰላም ለመግባት አመራሩና ሕዝብ እንዲሁም ሕዝብና ሠራተኛው ተባብሮና ተግባብቶ ለሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት መረባረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ዶ.ር መንገሻ አክለውም ሕዝባችን ለዘመናት ሊሟሉለት የሚሻቸው አንኳር ፍላጎቶች ያሉት በመሆኑ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ፍሬዎችን ለማግኘት መፈለጉ ተፈጥሯዊ ነው ያሉ ሲሆን ኾኖም ግን ሕዝባችን የሰላማዊ ትግል ተባባሪና ተሳታፊ በመሆን የሰላማዊ ትግል አማራጮች ላይ በመረባረብ ለእድገት ዘብ የሚቆም መሆን አለበት ነው ያሉት።ሕዝባችን ወደተሟላ ሰላም ይመጣ ዘንድ የአመራር አንድነት፣ የሕዝብ አንድነትና የዓላማ አንድነት ሊኖረን ያስፈልጋል ያሉት ዶ.ር መንገሻ ከፈተናዎች በላይ ሁነን ረዥም ጊዜያትን በድል ተጉዘን እዚህ የደረስን እንደመሆናችን ዛሬም ፈተናዎችን ተቋቁመን ማለፍ የሚያስችል አቅም አለን ብሎ በማመን ተግቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የመንግሥት የተግባቦት ተቋምን እንደሚመራና ለተግባቦትም እንደሚሠራ ኃይል ያለ ተግባቦት የሚፈታ ችግር እንደሌለ ተገንዝቦ ሕዝብን ከመንግሥት፤ መንግሥትን ከሕዝብ ጋር በተሳለጠ ግንኙነት በማስተሳሰር ለውጤታማነት መረባረብም ያስፈልጋል ብለዋል። መረጃው የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተያዘው የመኸር ወቅት ከ17 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት መታረሱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ ።
Next articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo: Hagayya 30/2015