“ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም ዘብ በመቆም የሀገርን ሰላም አስጠብቀን ልንዘልቅ ይገባል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው

67

ባሕር ዳር: ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁመራ ከተማ ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር የውይይት መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በውይይቱም ከፍተኛ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች ፣ የዞን የሥራ ኀላፊዎችና የመንግሥት ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን ብርጋዴል ጀኔራል ወርቅነህ ጉደታ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለው ጠንካራ ድጋፍና ደጀንነት የሚደነቅ መኾኑን ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብን ሰላም ለማጽናትና የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ደምና አጥንቱን እየገበረ የሀገርን ሉዓላዊነት እያስጠበቀ ይገኛል ያሉት ብርጋዴል ጄኔራል ወርቅነህ ጉዴታ መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ስብሰብ ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የሰላም አማራጮችን መዘርጋቱን ገልጸው የሕዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

ብርጋዴል ጄኔራል ወርቅነህ እንዳሉት የአማራ ሕዝብን ወደ ጦርነት በማስገባት የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለማጥፋት፣ ክልሉን የጦርነት ቀጣና በማድረግ በኢኮኖሚ እንዲደቅ የሚሠሩ ኀይሎች አሉ፡፡ የሀገርን ሰላም የሚያደፈርሱ ኀይሎችን በመቆጣጠር የሀገርን ሰላም ለማምጣት የሀገር መከላከያ ሠራዊት በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠንካራ ደጀን መኾናቸውን አስታውሰዋል። የሰላም እጦት ኢኮኖሚ የሚያደቅቅ በመኾኑ ሁሉም ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል ያሉት የመንግሥት ሠራተኞቹ መንግሥት ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

የመንግሥት ሠራተኞቹ የአማራ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ የኾኑት የወልቃይት የራያና ጠለምት የማንነት ጥያቄዎች በትኩረት ሊታዩ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማስተካከል የሰላም ውይይት አስፈላጊ ነው ያሉት የመንግሥት ሠራተኞቹ የሰላም አማራጮችን በማቅረብና ከሕዝቡ ጋር በመወያየት ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረ እግዚአብሔር ደሴ የአማራ ሕዝብ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠንካራ ደጀን በመኾኑ አሁን ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ስም ለማጠልሸት የሚሠሩ አካላትን ሊያጋልጥ ይገባል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ነጻነት መስዋእትነት መክፈሉን ያነሱት አቶ ገብረ እግዚአብሔር ሕብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ ሊያስቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” ዘብ በመቆም የሀገርን ሰላም አስጠብቀን ልንዘልቅ ይገባል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ዘብ ዋልታና ማገር በመኾኑ ከመቸውም ጊዜ በላይ ሕዝባችን ለሠራዊቱ ክብር ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

የዞኑ ሕዝብ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ያገኘውን ነጻነት አስጠብቆ ለመዝለቅ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በቅንጅት ሲሠራ መቆየቱን ያነሱት አቶ አሸተ አሁንም የተገኘውን አስተማማኝ ሰላምና ነጻነት አስጠብቆ ለመዝለቅ በቁርጠኝነት እንሠራለን ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለመጪው የዘመን መለወጫ በዓል በቂ የምርት አቅርቦት ወደ ገበያው ለማሰራጨት ዝግጅት ማጠናቀቁን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
Next articleበተያዘው የመኸር ወቅት ከ17 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት መታረሱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ ።