
ባሕር ዳር: ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕግን ከማስከበርና ሰላምን ከማስፈን በተጓዳኝ ለልማት እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አባል ሌተናል ኮለኔል በላይነህ በለጠ ገለጹ።
መከላከያ ሠራዊቱ በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን የሰብል ማሳ ከአረም የማፅዳት ሥራ አከናውኗል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አባልና የአልብኮ ወረዳ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ኮለኔል በላይነህ በለጠ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ መከላከያ ሠራዊቱ ለግዳጅ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ሁሉ ኅብረተሰቡን ያገለግላል፡፡
ሠራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበር እያስከበረ ግዳጁን በድል ከመወጣት በተጓዳኝ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሕዝባዊነቱን በተግባር የሚያረጋግጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን ገልጸዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ተገኝቶ የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን ሰብል ከአረም የማጽዳት ሥራ ማከናወኑን ጠቅሰው፤ በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
ኅብረተሰቡም አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ ደጀን ሆኖ ድጋፉን በማጠናከር ለሠራዊቱ ያለውን ፍቅር በተግባር እያረጋገጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከሠራዊቱ አባላት መካከል መሰረታዊ ወታደር ደሴ ግዛቸው በሰጡት አስተያየት፤ በአጥንትና በደማችን ሀገርና ሕዝብ ከመጠበቅ በጉልበታችንና በገንዘባችን ሕዝባችንን እያገለገልን እንገኛለን ብለዋል፡፡
ዛሬም የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች የሰብል ማሳ ከአረም የማጽዳት ሥራ ማከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ለሌላው ማኅበረሰብ አገልግሎት በመስጠት አብሮነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
ሰብሉ ሲደርስም ለማጨድና ለመውቃት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ሕዝባችን ከጎናችን ተሰልፎ ሁለተናዊ ድጋፍ በማድረግ ድጋፍ እየሰጠን ተጨማሪ አቅም ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደመቀ አድማሱ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በዞኑ ከ419 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ለምቶ የአረም ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እስካሁን በ100 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል ከአረም መጽዳቱን ጠቁመው፤ ምርታማነትን ለማሳደግ ሰብሉን ከአረምና ተባይ የመጠበቅ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
በተለይ መከላከያ ሠራዊቱ ህግ ከማስከበር ባለፈ የአቅመ ደካሞችን ሰብል ከአረም በማጽዳት ሕዝባዊነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።
አቅመ ደካማ በመሆናቸው በመኽር ወቅቱ በአንድ ሄክታር ማሳ ያለሙት ጤፍና ገብስ በአረም ተወሮ የቆየውን መከላከያ ሠራዊቱ ባደረገላቸው ድጋፍ መጽዳቱን የገለጹት በአልብኮ ወረዳ የ015 ቀበሌ አርሶ አደር ደርብ አራጋው ናቸው። በዚህም እፎይታ ማግኘታቸውንና ለተደረገላቸው እገዛም ምስጋና አቅርበዋል።
ሰብልን ከአረም በማጽዳቱ ሥራ ላይ ከመከላከያ ሠራዊቱ በተጨማሪ የደቡብ ወሎ ዞንና የአልብኮ ወረዳ አመራሮችም መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በደቡብ ወሎ ዞን ዘንድሮ በመኸር ከለማው መሬት 13 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከግብርና መምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!