የአገልግሎት አሠጣጥ ክፍተትን ለመሙላት እና የተሻለ ለማድረግ ግምገማዎች መካሄዳቸውን የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

84

ባሕር ዳር: ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአገልግሎት አሠጣጥ ክፍተትን ለመሙላትና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በክልል ደረጃ ግምገማዎች መካሄዳቸውን የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የአማራ ከልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ታደለ ልይለት ወቅቱ ዓመታዊ አፈጻጸም የሚገመገምበት እና ዕቅድ የሚተዋወቅበት ጊዜ ቢኾንም በተፈጠረው ወቅታዊ ችግር ሥራው በተፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ እንቅፋት ኾኗል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን በ2015 ዓ.ም የነበረውን የአገልግሎት አሠጣጥ ክፍተት የገመገመ ቢኾንም ግምገማውን ወደ ፈጻሚው ለማውረድ የሰላሙ ጉዳይ እክል ፈጥሯል ብሏል፡፡

በየደረጃው ያሉ አካላት በአገልግሎት ሠጪ ተቋማት ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሠሩ መኾኑንም የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ጠቁመዋል፡፡ ኮሚሽኑ የተሻለ ድጋፍ እና ክትትል ለማድረግ አቅዷል የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ከላይ እስከ ታች ያሉ ተቋማት ዕቅዱን ወስደው የሚሠሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ማኅበረሰቡ የሚያነሳው ጥያቄ በሁለት መንገድ ይፈታል የሚሉት አቶ ታደለ የመጀመሪያው በየደረጃው ባሉ ተቋማት እና አስፈጻሚዎች ሁለተኛው በሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ድጋፍ እና ክትትል እንደኾነ ጠቅሰዋል፡፡ ኮሚሽኑ ችግሮች የሚፈቱበትን ሁኔታ ከክልሉ ተቋማት ጋር ውይይት አድርጓል ብለዋል፡፡

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ተቋማትን መቆጣጠር እና መከታተል የሚችሉ እናት መሥሪያ ቤቶች መኾናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ችግሮች በተዋረድ እንደተገመገሙ ያነሱት አቶ ታደለ ኮሚሽኑ የአገልግሎት አሠጣጡ ቀልጣፋ እና ውጤታማ የሚኾንበትን መንገድ እያመቻቸን ነው ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡ የሚያነሳውን ችግር የዳሰሳ ጥናት በማድረግ እና በሌሎች ዘዴዎች በማጣራት በየደረጃው ላሉ አካላት ውጤቱ ለውይይት ቀርቧል ያሉት አቶ ታደለ ወደ ፈጻሚው ለማድረስ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ አስቸጋሪ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሪፎርሙን መሠረት በማድረግ በየሩብ ዓመቱ እየገመገመ አቅጣጫ እያወረደ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ 53 የክልል ተቋማት አሉ የሚሉት አቶ ታደለ 48 ተቋማት ጋር ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡

አሁን ያለው ችግር አገልግሎት ሠጪውም ኾነ አገልግሎት ፈላጊው በአግባቡ እንዳይገናኙ አድርጓል፤ በሥራውም ላይ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ ይኽን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ሰላም የኹሉም መሠረት ነው የሚሉት ኀላፊው ያለሰላም አገልግሎት መሥጠትም አገልግሎት ማግኘትም አስቸጋሪ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ2016 የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ምዝገባ ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አስታወቀ፡፡
Next articleየአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለጸጥታ አመራሮች ሹመት ሰጠ፡፡