
ባሕር ዳር: ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ፍታለሽ ምህረቴ እንደተናገሩት በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በክረምት የሚከናወኑ ተግባራትን በታቀደው መሰረት ተከናውነዋል፡፡
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ስር ያሉ ወረዳዎች ያሉበትን ሁኔታ ያገናዘበ በሶስት ዙር የተካሄደ ክትትል እና ድጋፍ መደረጉንም ምክትል መምሪያ ኀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የትምህርት ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ በማዘጋጀት ለወረዳዎች አቅጣጫ መሥጠቱም ተገልጿል፡፡
ወረዳዎችም የንቅናቄ መድረክ እንዲያዘጋጁ መግባባት በመደረሱ መድረኩን ለማዘጋጀት ሂደት ላይ መኾናቸው ታውቋል፡፡ ቀድመው የጀመሩ ወረዳዎች መኖራቸውንም ምክትል መምሪያ ኀላፊዋ አንስተዋል፡፡
ወይዘሮ ፍታለሽ እንዳሉት ለአዲሱ የትምህርት ዘመን መማሪያ ክፍሎች ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ እንዲኾኑ የሚያስችሉ ተግባራትም ተከናውነዋል፡፡
መማሪያ ክፍሎችን ማደስ፣ ቀለም መቀባት ፣ ፣የትምህርት ቤቶችን ግቢ ማጠር ፣ ማጽዳት እና የማስዋብ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ በዚህም ለ217 የመማሪያ ክፍሎች ቀለም የመቀባት ፣ የማደስ እና ጥገና የማድረግ ተግባር ተከናውኗል ብለዋል፡፡ ለ1 ሺህ 466 የመማሪያ ወንበሮች ፣ ለ28 መጸዳጃ ቤቶች፣ ለ25 ኮምፒውተሮች ፣ ለ158 የጥቁር ሰሌዳዎች እና የ1 ሺህ 360 ሜትር አጥር ጥገና ተደርጓል፡፡
እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የ2016 ትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ነሐሴ 27/2015 ዓ.ም እንደሚጀመር ኀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ዕቅድ 184 ሺህ 321 የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን እና 38 ሺህ 94 ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ይመዘገባሉ፡፡ ዕቅዱ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በስጋት ቀጠና ያሉ ትምህርት ቤቶችን ታሳቢ ያደረገ መኾኑን ምክትል ኀላፊዋ አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፋሲካ ዘለዓለም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!