
ባሕር ዳር: ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በመጪው የ2016 ዓ.ም የበጋ ወቅት ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያለፈውን የክረምት ወቅት ግምገማ እና በመጪው በጋ የሚኖረውን የአየር ትንበያ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ትናንት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በመጪው በጋ ወቅት ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። እንዲሁም የምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው የአየር ሁኔታ ትንበያ ያሳያል።
በአሁኑ ወቅት እየተስተዋሉ ከሚገኙት የአየር ሁኔታ ክስተቶች በመነሳት በሰሜን፣ በመካከለኛው፣ በምስራቅና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖርም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን በሰሜን ምስራቅ፣ መካከለኛውና በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ከ5 ዲግሪ ሴልሽየስ በታች እንደሚሆንም በትንበያው ማመላከቱንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ኢንስቲትዩቱ ባለፈው የክረምት ወቅት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደተስተዋለባቸው አውስተው፤ ይህም ለአርሶ አደሩ የግብርና እንቅስቃሴን ለማከናወንና የተፋሰሶችን የውሃ አቅርቦት በማሻሻል ረገድ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በመካከለኛው፤ በሰሜን ምስራቅ፣ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከዘነበው ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ጋር ተያይዞ የጎርፍ ክስተት ማጋጠሙን አውስተው፤ ይህም በትንበያው እንደተጠበቀው መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ፈጠነ ኀብረተሰቡ በበጋ ወቅት የሚጠበቀውን አየር ጠባይ ትንበያን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና የሚገኘውን የዝናብ መጠንና ስርጭት በአግባቡ በመጠቀም በወቅቱ የሚካሄደውን የግብርና እንቅሰቃሴ እና ሌሎች ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር ማከናወን እንዳለበት ተናግረዋል።
አልፎ አልፎ ከሚኖረው ከባድ ዝናብ ጋር በተያያዘ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑት ረባዳማና የወንዝ ዳር አካባቢዎች አስፈላጊውን የጥንቃቄ ሥራ ከወዲሁ ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ መለስ መኮንን በበኩላቸው፤ የሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በየጊዜው የሚሰጠው ትንበያ በተለይም ለግብርናው ሥራ ወሳኝ መሆኑን ተናግረው፤ በሚሰጠው ትንበያ መሠረት ቅድመ ዝግጅት የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በክረምት ወቅት በተሰጠው ትንበያ መሠረት ለግብርናው እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ዝግጀት በማድረግ ከ15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን የተቻለ መሆኑን አውስተው፤ አሁንም የዘር ጊዜ የሚከናወንባቸው አካባቢዎች ላይ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በትንበያው መሠረት የዝናብ እጥረት ለሚኖርባቸው አካባቢዎችን የውሃ አማራጭ የመጠቀም እና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ምርቶችን እንዲያለሙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ በክረምቱ ወቅት የእርጥበት መጠኑ ጥሩ ስለነበር እንደ ተምች ያለ የተባይ ክስተትን በቀላሉ መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።
የሚሰጠውን የአየር ሁኔታ ትንበያም ግምት ውስጥ በማስገባት በግብርና እንቅስቃሴው የተሳካ አፈጻጸም እንዲኖር በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!