
ባሕር ዳር: ነሐሴ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፋሲሎ ክፍለ ከተማ ሥራና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሃም ቢራራ እንዳሉት በክፍለ ከተማው በአምራች፣ በአገልግሎት እና በግብርና ዘርፎች ለተደራጁ 63 ኢንተርፕራይዞች የመሥሪያ ቦታ ርክክብ ተደርጓል፡፡
ኢንተርፕራይዞቹ 143 አባላት ያላቸው ሲኾን 6 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ርክክብ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ቦታው ከዚህ በፊት ለሌሎች የተደራጁ ወጣቶች ተሠጥቶ እንደነበር የገለጹት ኀላፊው በሽግግር እና በራሳቸው በወሰዱት አማራጭ ለአዲስ ሥራ ፈላጊዎች እንዲተላለፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ለኢንተርፕራይዞች የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመሥጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግም አንስተዋል፡፡
የመሥሪያ ቦታ የተረከቡ ኢንተርፕራይዞች ከዚህ በፊት ከሌላ ኢንተርፕራይዝ ተቀጥረው ይሠሩ እንደነበር ነግረውናል፡፡ በተሰጠው ቦታ በቀጣይ አምስት ዓመታት የተሻለ ሥራ በመሥራት ለቀጣይ ኢንተርፕራይዞች ለማስረከብ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የተቋማት ግብዓትና አቅርቦት የሥራ ሂደት የሼድ አሥተዳደር ባለሙያ ታየ መላኩ እንዳሉት ደግሞ በ2015 በጀት ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ ለሥራ እድል መፍጠሪያ የሚውል 18 ሄክታር መሬት የልየታ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ለአምራች ዘርፍ፣ ለከብት እና ዶሮ እርባታ፣ ለጣውላ ሥራ፣ ለባልትና እና ለተለያዩ ዘርፎች እንደሚውልም ነው የገለጹት፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ በውላቸው መሠረት እንዲሠሩ ክትትል ይደረጋልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!