
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በማሽላ ሰብል ላይ የተከሰተው የግሪሳ ወፍ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ዮርዳኖስ የሽዋልዑል ከ940 ሄክታር በላይ ማሳ የማሽላ ሰብል ሙሉ በሙሉ መውደሙን ገልጸዋል።
በወረዳው 14 ቀበሌዎች በተከሰተው የግሪሳ ወፍ በ3 ሺህ 792 አርሶ አደሮች የማሽላ ሰብል ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሶባቸዋል።
አርሶ አደሮቹ የተበላውን ማሽላ መሬት ቀይ ሽንብራ ለመዝራት እንቅስቃሴ ላይ መኾናቸውን አስረድተዋል።
በጥሩ ቁመና ላይ ይገኝ የነበረው ሰብል ጉዳት ቢደርስበትም የተረፈውን ለመከላከል ከግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል አቶ ዮርዳኖስ።
በፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈፃሚ በላይሁን ንጉሴ የኬሚካል እርጭት ለማድረግ የተዘጋጀ አውሮፕላን ስላለ እርጭት ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።
የኬሚካል ርጭት ለማድረግ ማኅበረሰቡ ከግብርና ሥራው ጎን መኾን እንዳለበት ነው የጠቆሙት።
በወረዳው እና በፌዴራል በኩል የኬሚካል እርጭቱ ቢደረግ የሚያሰጋ የጸጥታ ጉዳይ እንደሌለ ማሳወቃቸውንም ነው ያብራሩት።
ወረዳው የማሽላ ሰብልን ጨምሮ በጤፍ ሰብል በሰፊው ይታወቃል።
ዘጋቢ፡- ወንዲፍራ ዘውዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!