“በበጀት ዓመቱ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተከናወኑ ሥራዎች ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ ተተክተዋል” ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

44

ባሕር ዳር: ነሐሴ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተከናወኑ ሥራዎች ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

በ2015 ዓ.ም የሀገሪቷ የማምረት አቅም 55 በመቶ መድረሱንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሪዎችና ሠራተኞች የተሳተፉበት የ2015 ዓ.ም የዘርፉ የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የአዲሱ በጀት ዓመት የሴክተሩ ዋና ዋና ግቦችን ማሳካት በሚቻልበት ሂደት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት በ2015 በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችና የአምራች ዘርፉን የማምረት አቅም ከማሳደግ አንፃር ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በተለይም የአምራች ዘርፉ እርስ በራሳቸው የገበያና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ትስስር እንዲኖራቸው፣ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ የአምራቹን ግንዛቤ ከማጎልበትና በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በመደገፍ ረገድ የተሻለ ሥራ መሠራቱን አመልክተዋል።

በተጨማሪም የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከመሳብ አንፃር አበረታች ውጤት የተመዘገበበት የበጀት ዓመት መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 55 በመቶ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

በተለይም ለውጭ ገበያ የሚኾኑ ምርቶችን ማሳደግ፣ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እንዲሁም በዘርፉ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ አበረታች ውጤት የተገኘበት ዓመት ነበር ብለዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በዚህም ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸውን ገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን አቶ መላኩ አመልክተዋል።

የመድረኩ ዓላማ የሚንስቴሩ መሪዎችና ሠራተኞች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኙ ስኬቶችን በአግባቡ በመገንዘብና የታዩ ክፍተቶችን በመለየት የ2016 ዓ.ም ዋና ዋና ግቦች ላይ ተገቢውን ግንዛቤና ክህሎት አግኝተው ለተፈፃሚነታቸው በሙሉ አቅማቸው እንዲረባረቡ ለማዘጋጀት መሆኑንም አመልክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመንግሥት ዲጂታል የግዥ ካርድ ይፋ ሆነ።
Next articleየትምህርትን ቤቶችን ገጽታ በመቀየር የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ መከናወናቸውን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ገለጸ።