
ባሕር ዳር: ነሐሴ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጋራ ፕሮጀክት የሆነው የመንግሥት ዲጂታል የግዥ ካርድ ይፋ ሆነ።
በፌዴራል የመንግስት ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አተገባበር ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖን ጨምሮ የመንግስት ተቋማት የፋይናንስ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዕለቱ ይፋ የሆነው የመንግሥት ዲጂታል የግዥ ካርድ፤ ተቋማት የዲጂታል ግዥ ለመፈጸም የሚያስችል ሲሆን የመንግስት ወጪ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ነው።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ170 በላይ የሚሆኑ ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርዓት የገቡ ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 3 ትሪሊዮን የገንዘብ ግብይት መፈፀሙ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርዓት በአጭር ጊዜ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ 3 ነጥብ 3 ትሪሊዮን በዲጂታል ግብይት በኩል ገንዘብ መንቀሳቀሱን ገልጸዋል።
የዲጂታል ግብይት ስርዓት ማለማመድ ረጅም ጊዜ ፈተና ሆኖ ቢቆይም፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ በመንግስት ከመጣ በኋላ ትልቅ ለውጥና መነቃቃት አምጥቷል ብለዋል።
በዕለቱ ይፋ ከሆነው የመንግሥት የግዥ ካርድ በተጨማሪ ሌሎች የክፍያ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አሰራሮች እንደሚጀመሩ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የግዥ ካርድ ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አንዱ ቁልፍ ዘርፍ የዲጂታል ሽግግር ዕውን ማድረግ መሆኑን ገልፀው፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂን ዕውን ለማድረግ ብዙ ርቀት መኬዱን ተናግረዋል።
በመንግሥት የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶለት ወደ ሥራ የተገነባና የሕግ መሰረት ያለው የዲጂታል ስትራቴጂ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ነው ያነሱት።
በዚህም የመንግስት ክፍያ ስርዓትን በኤሌክትሮኒክ ግብይት ማስገባት አንዱ ዋነኛ ስራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የመንግሥት ግብይት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስርዓት ትልቅ ድርሻ ስላለው ከባንኩ ጋር በጋራ የሚሠሩ ሥራዎች ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ነው ያሉት።
የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ዕውን ማድረግ የክፍያ ስርዓትን ከማሻሻል ባለፈ የፋይናንስ ተጋላጭነት በመቀነስ በኩል ፋይዳው የጎላ ነው።
በሂደትም አጠቃላይ የዲጂታል ስርዓትን በማስፋፋት ይህ አገልግሎት ከሌሎች ባንኮች ጋርም ክፍያ መፈፀም የሚያስችል እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።
በየጊዜው የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተሻለ አገልግሎት ማቅረብ ይገባል ያሉ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት ወደዚህ ዘመናዊ አሰራር እንዲገቡ አሳስበዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው በበጀት ዓመቱ በዲጂታል አገልግሎት የተሻለ አፈፃፀም የነበራቸው ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!