
ባሕር ዳር: ነሐሴ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አሥተባባሪ ዓብይ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው ጉባኤ የ18ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መነሻ ዕቅድ ላይ ተወያይቷል።
በዓሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሥተባባሪነትና በሱማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት በጅግጅጋ ከተማ “ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በድምቀት እንደሚከበር አሥተባባሪ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
ዓብይ ኮሚቴው በሐገር አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ፣ በሱማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት ለ2ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ብዝኃነታችንን እና እኩልነታችንን በመቀበል ሐገራዊ አንድነታችንን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚከበር ገልጿል።
የዓብይ ኮሚቴውን ስብሰባ የመሩት የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የሕዝቦችን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ትስስር በማጠናከርና በሕገ መንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
በዚህ ዓመትና በቀጣይ በሚከበሩት በዓላት ላይም እነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በሐገራችን የሕግ የበላይነት እስኪከበርና ሕገ መንግሥታዊነት ባሕላችን እስኪሆን ድረስ በትጋትና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አቶ አገኘሁ አያይዘውም ሕዳር 29 ሕገመንግሥቱ የጸደቀበትንና ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የተረጋገጠበትን ቀን ለመዘከር የሚከበረው ይህ በዓል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ለማስከበር ፣ የብዝኃነት አያያዛችን እንዲጠናከር ፣ አብሮነትና ወንድማማችነት ሥር እንዲስድና የፌዴራል ሥርዓቱ እንዲጎለብት ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በዓሉ ለፍትሕ፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችና ምክክሮች በሰፊው እንደሚካሄዱ አስረድተዋል። መረጃው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!