
ባሕር ዳር: ነሐሴ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፤ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፤ 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔውን ሲያካሂድ በክልሉ ርእሰ መሥተዳድር የቀረቡትን ሹመቶች ማጽደቁ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎም በአዲስ የተቋቋመው የክልሉ ካቢኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው፡፡
በርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሚመራው የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያደረገ ነው፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት ሐምሌ ላይ ባካሔደው ጉባዔ የአማራ ክልልን የ2016 በጀት መርምሮ ማጽደቁ ይታወሳል፡፡
የምክር ቤቱን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በክልል ደረጃ የባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን የ2016 በጀት ዓመት በጀትን አስመልክቶ የተለያዩ ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
አዲሱ ካቢኔም ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ያቀረቡትን መነሻ እቅድ በዝርዝር በማየት የክልሉን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን በሚያግዝ መልኩ የበጀት ድጋፍ እረቂቅን እየተመለከተ ነው፡፡
የመሥተዳድር ምክር ቤቱ የሚያየው ሌላኛው አጀንዳ የ2016 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹ የደረሱበትን ደረጃ ነው፡፡ መምህራን፣ ርእሳነ መምህራን እና የትምህርት ሱፐርቫይዘሮች የተማሪዎች ምዝገባን በተቀመጠለት የጊዜ መርሐ ግብር በየትምህርት ቤቶቻቸው ተገኝተው እንዲያካሂዱ የሚያስችል ግምገማ አካሂዶ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!