
አዲስ አበባ: ነሐሴ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የግማሽ ዘመን ግምገማ ውይይት እየተካሄደ ነው። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና ማኅበረሰብ ለመቀየር ያስችላል ተብሎ የቀረበ የመንግሥት እቅድ መኾኑን በለጠ ሞላ (ዶ.ር) በመክፈቻው ተናግረዋል ።
ስትራቲጂው ከሀገራችን የልማት ራዕይ ፣ የፖሊሲ ዓላማዎች እና ቅድሚያ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ጋር ተሰናስሎ እና በወቅቱ የነበሩ ዓለም አቀፋዊ ፣ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮችን አካቶ እንዲረቅቅ ተደርጎ ሰኔ 8 ቀን 2012 በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀ ሀገራዊ ዕቅድ ነው ብለዋል፡፡የስትራቴጂው የመጨረሻ ግብ የሀገራችንን የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት በማረጋገጥ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ፣ ሀገራዊ ገቢን መጨመር እና አካታች የኾነ ብልጽግና እንዲረጋገጥ በማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ህይወት እንዲሻሻል ማድረግ ነው። እነዚህን ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ስትራቴጂው በተለይም በኢትዮጵያ የዲጂታል መሰረቶችን በማልማት ላይ ያተኩራል ነው ያሉት ።
የዲጂታል መሰረቶች ቀጣይነት ያለው የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት መሰረት የሚጥሉ ናቸው። የስትራቲጂው ዋና እሳቤ እነዚህን የዲጂታል መሰረቶቸ እንደ ሀገር ማልማት ካልቻልን በየትኛውም ዘርፍ በዲጂታል የታገዘ ልማትን በተሟላ ኹኔታ ማካሄድ አንችልም የሚል ነው። የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መሰረቶች ውስጥ፣ የቴሌኮም እና ተያያዥ መሰረተ ልማቶች፤ የዲጂታል መታወቂያ፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እና የሳይበር ደህንነት የመሳሰሉ የዲጂታል ማስቻያ ፕላት ፎርሞች ፤ ተጠቃሚዎች አገልግሎት በቀጥታ የሚያገኙባቸው የኢኮሜርስ እና የኢመንግሥት ፕላትፎርሞች ፤ የዲጂታል ክህሎት እና ዕውቀት፣ ለነባር እና አዳዲስ የዲጂታል ተቋማት በቀላሉ የሚገኝ የፋይናንስ ምንጭ፣ እና ለዲጂታል ኢኮኖሚው ሂደት የሚያሳልጡ የሕግ እና የቁጥጥር ማዕቀፎች ይገኙበታል ሲሉ ተናግረዋል ።
ስትራቴጂው የዲጂታል መሰረቶችን ከማልማት አንጻር ያሉ ችግሮች ምን እንደነበሩ ለይቶ በማስቀመጥ ችግሮቹን ለመፍታት ሊተኮርባቸው የሚገቡ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በዝርዝር አስቀምጧል። በተጨማሪም በመፍትሔት የተቀመጡ አቅጣጫዎች አካታችነትን መሰረት አድርገው እንዲተገብሩ ከግምት መግባት ያለባቸውን ጉዳዮች ለይቶም አስቀምጧል። በተመሳሳይ ኹኔታ ትኩረት ሊሰጣቸወ በሚገቡ ዘርፎችም በአፋጣኝ መሥራት ያለባቸውን ዋና ዋና ሥራዎች እና የአፈጻጸም አግባቦችን ለይቷል ብለዋል።
ውይይቱ ለ2 ቀናት የሚቆይ ሲኾን ባለድርሻ አካላትና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
